የዛሬ 30 ዓመት... ግንቦት 8፣ የነፍስ ውጭ፣ ነፍስ ግቢ ዕለት

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
selam sew
Leader
Leader
Posts: 692
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

የዛሬ 30 ዓመት... ግንቦት 8፣ የነፍስ ውጭ፣ ነፍስ ግቢ ዕለት

Unread post by selam sew »

የዛሬ 30 ዓመት... ግንቦት 8፣ የነፍስ ውጭ፣ ነፍስ ግቢ ዕለት
Image

የዛሬ 30 ዓመት... የኮ/ል መንግሥቱ አውሮፕላን ለምን አልጋየም?

የዛሬ 30 ዓመት፣ ማክሰኞ'ለታ የወጣችው ጨረቃ "ጤፍ ታስለቅም ነበር"። ሌ/ኮ ካሳዬ ታደሰ ናቸው እንዲያ የሚሉት። እንደ ትናንት ያስታውሷታል፤ የነፍስ ውጭ-ነፍስ ግቢ ሌሊት። እርሳቸው ያኔ የ102ኛው አየር ወለድ ኢታማዦር ሹም ነበሩ።

30 ዓመት ብዙ ነው። ግንቦት 8 የኾነው ግን ዛሬም ድረስ እንቆቅልሽ ነው። እንደው በደፈናው "ተምኔታዊም ተውኔታዊም" ነበር ማለቱ ይቀል ይሆን?

የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹሙ ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ 'የኢትዮጵያን ባንዲራ ራሳቸው ላይ ጠምጥመው' ምናልባትም እንደ 'መይሳው ካሣ' ሽጉጣቸውን የጠጡባት ምሽት።

እርግጥ ነው በጄኔራል መርዕድ ዙርያ ብዙ የሚጣረስ ታሪክ አለ። ባንዲራ ለብሰው ነበር ከሚለው ሰነድ አልባ ተረክ ጀምሮ እስከ አሟሟታቸው ድረስ ይኸው 30 ዓመት እንኳ ያልፈታው ምሥጢር...።

ሻምበል እዮብ አባተን እዚህ ጋ እናምጣቸው። ያኔ የወታደራዊ ደኅንነት ባልደረባ ነበሩ። ከዚያ በኋላም ስለ መፈንቅለ መንግሥቱ ጥናት አድርገዋል። ስለ ጄኔራል መርዕድ አሟሟት በስፋት ከሚታመነው በመጠኑም ቢኾን ያፈነገጠ ታሪክ ጽፈው አስነብበዋል።

ጄኔራል መርዕድ ራሳቸውን ባጠፉ አፍታ እዚያ ደረስኩ ያለ አንድ የልዩ ብርጌድ ወታደር ነገረኝ ብለው ለቢቢሲ እደተናገሩት ከሆነ ጄ/ል መርዕድ ያን ምሽት ራሳቸው ላይ ቢተኩሱም ነፍሳቸው ወዲያውኑ አልወጣችም። ሺህ ወታደር ሲያዝዙ ኖረው ሞት አልታዘዝ አላቸው።

አምቡላንስ ተጠርቶ ቢመጣም አምቡላንሷ ወደ ሆስፒታል አልወሰደቻቸውም፤ ወደ ቤተመንግሥት እንጂ። አምቡላንሷ ውስጥ እስከ ንጋት ድረስ እያጣጣሩ ነበር። ቢያንስ ለ6 ሰዓታት፤ በሁለት ወታደሮች እየተጠበቁ ጣር...።

ነገሩ ሆን ተብሎ የተፈጸመ የጭካኔ ተግባር ይመስላል፤ አልያም ደግሞ ዘመኑ የወለደው የበዛ ፍርሃት። በዚያች የነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ቅጽበት ማን ደፍሮ የመፈንቅለ መንግሥትን አውራ አቀናባሪና ጎንጓኝ "ሕክምና ያግኙ!" ብሎ ይጮኻል?

'አንተን የነዚህ ከሐዲዎች ጠበቃ ማን አደረገህ? ብባልስ' ይላል የዐይን እማኙ ዝምታን ለምን እንደመረጠ ሲተርክ።

...በሥራ ስንዋከብ ቆይተን ወደ አምቡላንሷ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ስንመለስ 'የጄኔራሉ ህሊና የሚረብሸውና አንጀት የሚያላውሰው የጣርና የሲቃ ድምጻቸው ከበፊቱ ቀንሶ ይሰማ ነበር።'

አጭር የምስል መግለጫ

ብ/ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ 1975-1979 የኤርትራ አስተዳዳሪ እና የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት አዛዥ ሳሉ።

በዚህ ረገድ የአየር ኃይሉ አዛዥ ጄኔራል አምሐ ዕድለኛ ነበሩ ማለት ይቻላል። የሟችና የአሟሟት ዕድለኛ ካለው...። ጄ/ል አምሐ ሽጉጣቸውን መኪናቸው ውስጥ ረስተውት ነበር ወደ ስብሰባ የገቡት። ሽጉጥ ፍለጋ ተሯሯጡ። መከላከያ አንድ ቢሮ ዘው ብለው ሲገቡ ግድግዳ ተደግፎ የቆመ ክላሽ አገኙ። እስከ ወዲያኛው አሸለቡ። ጄ/ል መርዕድ እያጣጣሩ ከሚገኙበት አምቡላንስ ውስጥ፣ በሁለት የልዩ ብርጌድ ወታደሮች እየተጠበቀ ከነበረው አምቡላንስ ውስጥ የእርሳቸውም ሬሳ ተጠቅልሎ እንደነገሩ ተጋድሞ ነበር፤ እንደ ሻምበል እዮብ 'የማያወላዳ' የዐይን እማኝ ከሆነ።

ቢቢሲ፡- ሻምበል! ግን እኮ ይሄ ጄ/ል መርዕድን አሟሟት በተመለከተ የሚሉን ነገር እስከ ዛሬ ያልተሰማ ታሪክ ነው። ነገረኝ የሚሉትን ወታደር ያምኑታል?

ሻምበል እዮብ፡- የልዩ ብርጌድ ጥበቃ ጠባቂ ባልደረባ የነበረ ነው፤ ያን ምሽት ያየው ነገር እስከ ዛሬም ይረብሸዋል። ታሪክ ተዛብቶ ሲነገር ተበሳጭቶ ነው እኔን ያገኘኝ። ''እውነታውን አስተካክለህ ጻፍ፤ እኔ እዚያው የነበርኩ ወታደር ነኝ" ነው ያለኝ፡፡ በዚያ ምሽት እሱ እዚያ ስለመኖሩ ከሌሎች አረጋግጫለሁ።

ግንቦት 8፣ የነፍስ ውጭ፣ ነፍስ ግቢ ዕለት

አየር ወለዱ ጄኔራል አበራ አበበ የገዛ አለቃቸውን የመከላከያ ሚኒስትሩን ጄኔራል ኃይለጊዮርጊስን በሽጉጥ ገድለው፣ የዘበኛ ልብስ አስወልቀው፣ የወታደር ዩኒፎርማቸውን ቀይረው፣ ሲኒማዊ ኩነት በሚመስል አኳኋን አጥር ዘለው ከመከላከያ ግቢ ያመለጡበት ቀትር!

ይህም ታሪክ አሻሚ ነው። ለምን አመለጡ? ለምን ሚኒስትሩን ገደሉ? እንዴት መፈንቅለ መንግሥት የሚያህልን ነገር እየመሩ አንድ ሚኒስትር ስለገደሉ ብቻ እንደ ተራ ነፍሰ ገዳይ ሊያመልጡ ይችላሉ? 30 ዓመት ያልመለሳቸው ጥያቄዎች።

ግንቦት 8፤ የነፍስ ውጭ፣ ነፍስ ግቢ ዕለት

ጄኔራል ፋንታ በላይ ለሦስት ቀን-ሦስት ሌሊት ኮንቴይነር ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት የተደበቁበት ምሽት…።

ጄኔራል ፋንታ የትምህርት ዝግጅታቸውና የአመራር ብቃታቸው ለርዕሰ ብሔርነት አሳጭቷቸዋል። ምናልባትም ስዒረ መንግሥቱ ተሳክቶ ቢኾን ኖሮ ኢትዮጵያን የሚመሯት "ፕሬዝዳንት" ፋንታ በላይ ነበሩ።

ይህን የጄኔራል ፋንታ በላይን ድርጊት ተከትሎ 'ማሽሟጠጥ የሚቀናው' ሰፊው ሕዝብ ተቀኘ ተባለ…

_"ፔፕሲ ኮካ ኮላው ከከተማ ጠፍቶ_

_ፋንታ ተገኘ አሉ በኮንቴይነር ሞልቶ"_

በኤርትራ የማህበራዊ ድረ ገጾች አገልግሎት ተቋረጠ

ግንቦት 8፤ የነፍስ ውጭ፣ ነፍስ ግቢ ምሽት…

ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ በብዙ ጽናት፣ በብዙ ትጋት አምጣ ያዋለደቻቸው፣ ለወግ ማዕረግ ያበቃቻቸውን እጅግ ውድና ምትክ የለሽ የሚባሉ ጄኔራሎቿን በአንድ ጀንበር ያጣችበት…ምሽት።

አይደለም አገረ ኢትዮጵያ፣ አህጉር-አፍሪካ ሳትቀር ከተቀረው ዓለም ወራሪ ጦር ቢገጥማት ከፊት ልታሰልፋቸው የምትችላቸው ምርጥ ጄኔራሎቿ ነበሩ…።

ግንቦት 8 የኾነው በትክክል ምንድነው?

ጓድ ሊቀመንበር ምሥራቅ ጀርመንን ለመጎብኘት ክብርት ወ/ሮ ውባንቺንና ልጃቸውን ትዕግስትን (ወይም ትምህርትን) አስከትለው፣ በትረ መኮንናቸውን እየወዘወዙ ቦሌ ተገኙ። ረፋድ ላይ።

መንጌ ቆቅ ናቸው። ሆን ብለው ሰዓት ያዛባሉ። ጠላትን ለማወናበድ ወይ ረፈድ ወይ ቀደም ይላሉ። እርሳቸው ላይ የሚዶልተው ብዙ ነዋ።

ያን ለታም እንዲሁ አደረጉ። ማልጄ ነው 'ምሳፈረው ብለው ለደኅንነት ሚኒስትራቸው ተናገሩ። ሚኒስትሮቻቸው እውነት መስሏቸው ቦሌ ማልደው ደረሱ። እርሳቸው ግን ረፋድ ላይ ግንባራቸውን ቅጭም አድርገው ከቸች…።

ብዙዎቹ ጄኔራሎች እስከዚያች ሰዓት ድረስ ይቁነጠነጡ ነበር። ቶሎ ወደ ቢሮ መመለስ አለባቸዋ። አጣዳፊ ሥራ ነው የሚጠብቃቸው። መንጌን ወደ 'መንግሥተ ሰማይ' ልኮ መሬት ላይ አዲስ መንግሥት የማቆም ብርቱ ሥራ አለባቸው።

ጄኔራሎቹ ጦርነት ታክቷቸዋል። በመንጌ "ቆራጥ" አብዮታዊ አመራር ሺህ የድሀ ልጆችን መማገድ አንገሽግሿቸዋል፤ በአፋቤቴ፣ በቀይ ኮከብ፣ በባሕረነጋሽ ዘመቻ…አሥር ሺህዎች እንደቅጠል ረግፈዋል። 'ጦርነትን እንደ ሥራ የያዘ መንግሥት ሕዝብ ሊመራ እንዴት ይቻለዋል?' ሲሉ ነበር ድምጻቸውን ዝግ አድርገው የሚያጉረመርሙት።

መንግሥቱ ይሄን ማጉረምረም ከሰሙ ጄኔራሎቹን አይምሯቸውም። ማዕረጋቸውን በመቀስ፤ ግንባራቸውን በሽጉጥ ሊነድሉት ይችላሉ፤ አድርገውታልም። የናደው ዕዝ ዋና አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ታሪኩ ዓይኔን፣ አሳዛኝ ፍጻሜን የሰማ ከመንጌ ጋር አይቀልድም።፡

የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ደቋል፣ ሕዝብ ተርቧል፤ ወታደሩ ኮቾሮ እየበላ ነው የሚዋጋው። የገዛ ልጁንና ሚስቱን እንኳ ማየት አይፈቀድለትም። ጄኔራሎቹ 'የገዛ ወገናችንን ትርጉም በሌለው ጦርነት ለምን እናስጨርሳለን?'፣ 'ደግሞስ የሰሜኑ ችግር በፖለቲካ እንጂ በአፈሙዝ ይፈታል እንዴ?'…እያሉ ያጉረመርሙ ነበር፤…መንጌ ሳይሰሙ።

ኮ/ል መንግሥቱ ግን ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር እያሉ ጦርነቱን ገፉበት። በዚያ ላይ ከጦር አዛዦቻቸው ይልቅ ካድሬዎቻቸውን ማመን አበዙ።

"ይሄ ሰውዬ እኛን የማይሰማ ከሆነ ለምን አናስወግደውም?" አሉ…ጄኔራሎቹ፤ ማንም ሳይሰማቸው።

መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ ዝግጅት ተጧጧፈ። ለዚያ ነው ያን ቀን፣ ግንቦት 8 መንጌን ቶሎ መሸኘት የነበረባቸው…፤

ከሻዕቢያ ጋር ቶሎ ለድርድር መቀመጥ ያሻል። ይሄን የውጭውን ሽርጉድ፣ ገና ድሮ መንጌን የከዱት ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ አሰናድተውታል። ጄኔራሎቹ የመንጌን ወደ ምሥራቅ ጀርመን መሸኘት…ይቅርታ የመንጌን

እስከወዲያኛው መሸኘት በጉጉት እየጠበቁ ያሉት ለዚሁ ነው።

የዛሬ 30 ዓመት፤ ግንቦት 8፤ ረፋድ ላይ

ሰዓቱ አልገፋ አለ…

ወግ ነውና…መሪን መሸኘት… "ጓድ ሊቀመንበር በሰላም (አ)ይመልስዎ" እያሉ ቀኝ-ወ-ግራ ተሰይመው ተሰናበቷቸው፤ የገዛ ጄኔራሎቻቸው።

መንጌ ያቺን ተወርዋሪ ኮከብ የመሰለች ፈገግታቸውን ቦግ እልም እያደረጉ አጸፋውን መለሱ። ለምን ይሆን ግን ፈጣሪ ለአምባገነኖች ችምችም ያለ፣ የተፈለፈለ በቆሎ የሚመስል ጥርስና ረዥም ዕድሜን የሚቸረው?

የሚደንቀው ታዲያ…በዚያች ዕለት የቦሌ ሽኝት ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ አልተገኙም። ይሄ ቀላል ፕሮቶኮሏዊ ህጸጽ ተብሎ ሊታለፍ ይችላል። ጊዜ አጥተው ነው ሊባልላቸውም ይችላል…። ምክንያቱም ዘመኑ የጥድፊያ ነዋ…የጦርነት። በየግንባሩ ‹‹ገንጣይ-አስገንጣይን›› ለመፋለም የወገን ጦር ከሺህ "የወንበዴው ጦር" ጋር ተናንቆ እየተዋደቀ ነው። ፈንጂ እየረገጠ ነው…በእንዲህ ያለ ቀውጢ ጊዜ ለሽኝት መኳኳል ቅንጦት ሊሆን ይችላል። ቢኾንም…ጄኔራሉ ደግ አልሠሩም።

"መርዕድ ምነው ቀረ? ምንስ ብርቱ ጉዳይ ቢገጥመው፣ ቆራጡን መሪያችንን መሸኘት አልነበረበትም?" የምትል የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ ሳይገባቸው አልቀረም፤ የደኅንነቱን ሹሙን፤ ኮ/ል ተስፋዬ ወልደሥላሴን…።

ኢታማዦር ሹሙ ደግ አልሠሩም፤ እንደምንም ብለው አለቃቸውን መሸኘት ነበረባቸው። እርሳቸው በተቃራኒው መከላከያ ሚኒስትር ውስጥ፣ ከኢትዮጵያ ሆቴል ፊት ለፊት፣ ከአምባሳደር ሲኒማ ጎን፣ ከቢሯቸው ቁጭ ብለው የክፍለ ዘመኑን አስገራሚ የስዒረ መንግሥት 'ተውኔት' እየጻፉ ነበር።

የመንጌ አውሮፕላን ለምን አልጋየም?

ጓድ መንግሥቱ ለምሳ ያሰቧቸውን ለቁርስ ማድረግን ተክነውበት ሊሆን ይችላል። በዚያች ዕለት ግን ቁርስም ምሳም እራትም ሊደረጉ የነበሩት እርሳቸው ናቸው። ይህን ፈጽሞ አያውቁም። አውሮፕላኑን የተሳፈሩትም የእሳትራት ኾነው ነው።

የተሳፈሩባትን አውሮፕላናቸው ሰማይ ላይ እንዳለ የማጋየቱ ነገር ያበቃለት፣ ተቦክቶ ያለቀ፣ የደቀቀ ጉዳይ ነው። ይህን ያጸደቁት ደግሞ ከሞላ ጎደል ሁሉም የጦር አዛዦች ነበሩ። ድንገት መንጌን ሸኝተው ሲመለሱ ቆፍጣና ወታደራዊ መንፈሳቸው በ'ኖና ተ'ኖ የባህታዊ ሐሳብ በልባቸው አደረ።

"…ጓዶች! ለምን እናጋየዋለን ግን?"

"እንዴት ማለት…"

"...እሱን ለመግደል ብለን የ70 ንጹሐን ነፍስን ከምናጠፋ…."

"ኖኖኖኖ…ወደ ኋላ ባንመለስ ነው የሚሻለው በዚህ ጉዳይ…ተስማምተን የጨረስነውን? ''

"አደለም!ተስማምተን ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ወ/ሮ ውባንቺስ፣ ልጃቸውስ? አብራሪዎቹስ? ወገኖቻችን አይደሉም? ምን አጠፉና ነው በዚህ ሰውዬ ጦስ የሚጠፉት…" ይሄ ሐሳብ ምናልባትም ከአየር ኃይል አዛዡ ጄኔራል አመሃ የመጣ ሳይሆን አይቀርም።

"…እና ምን በጀ ጓዶች?" ምናልባት እርጋታ የማይለያቸው ሰብሳቢው ጄኔራል መርእድ እንዲያ ጠይቀው ይሆናል።

"…ባይሆን በጦር አውሮፕላን አስገድደን አሥመራ ብናሳርፈው አይሻልም?" ይሄ ከጄኔራል አመሃ የመጣ መፍትሄ ሊሆን ይችላል።

" አሥመራ የማይሆን ነው፤ በሙሉ መንጌ መንጌ የሚል አየር ወለድ ነው ያለው"

በዚህ ጊዜ ምናልባትም የዘመቻ አዛዡ ጄኔራል አበራ እምር ብለው እንዲህ ተናግረው ይሆናል፤ "ምንድነው ይሄ ውልውል? ተስማምተን? ተግባብተን በአንድ ያጸደቅነውን? የምን መንሸራተት ነው? ይሄኮ ፌዝ አይደለም! መፈንቅለ መንግሥት ነው እያካሄድን ያለነው። የሊቀመንበሩን አውሮፕላን ካላጋየን ኋላ የምንጋየው እኛው ነን…ውርድ ከራሴ…"

ጄኔራሎቹ መግባባት ተሳናቸው። ይህ ጉዳይ የመጨረሻቸው መጀመርያ ኾነ።

ጄኔራሎቹ በመከላከያ ሚኒስትር ግቢ፣ አንደኛ ፎቅ ላይ፣ ፊቷን ወደ ክቡ የብሔራዊ ባንክ ሕንጻ ባዞረች አንዲት የስብሰባ አዳራሽ ታድመው በኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ላይ እንዲህ ጉንጭ አልፋ ክርክር እያደረጉ ሳለ ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱን የያዘው አውሮፕላን በሰማይ ላይ ሳይጋይ፣ አሥመራም ተገዶ ሳያርፍ የኢትዮጵያን የአየር ክልል እየቀዘፈ ራቀ።

ደብረዘይት አየር ኃይል ግቢ አውሮፕላኑን ለመምታት በተጠንቀቅ የነበሩት ጄቶችም ሞተር አጠፉ።

አጭር የምስል መግለጫ

ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ

በአሥመራ ግን 'መንጌ ተገድለዋል'

በአሥመራ የግዙፉ 2ኛው አብዮታዊ ሠራዊት አድራጊ ፈጣሪ፣ ሥመ ጥሩው ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ ናቸው። እንዲያውም የስዒረ መንግሥቱ ሁነኛው ጠንሳሽ ሳይሆኑ አይቀሩም።

ምክትላቸውን ጠርተው ነገሩ ሁሉ መልክ መልክ መያዙን አረጋገጡ። ጄኔራል ቁምላቸው በአራት አንቶኖቭ የታጨቁ 433 ልዩ ኮማንዶዎችን አሳፍረው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ እንዲጀምሩ አዘዟቸው።

ጄኔራል ቁምላቸው አገሪቱ አለኝ የምትላቸውን የአየር ወለድ አባላት "ዳይ! ተንቀሳቀስ" አሏቸው። በወታደር ቤት አለቃ ሲያዝ "አቤት ጌታዬ!" እንጂ "ለምን ጌታዬ?" አይባልም።

ሶቭየት ሠራሽ አንቶኖቭ ውስጥ እንዳሉ ድንገት ጄ/ል ቁምላቸው እመር ብለው ተነሱ። የሃሎ ሃሎ መነጋገሪያውን ረዳታቸው አቀበሏቸው። አንድ በራሪ ወረቀት ከኪሳቸው አውጥተው ማንበብ ጀመሩ።

መንጌ ተገድሏል። ጦርነት አብቅቷል። እንኳን ደስ ያላችሁ!

ቁምላቸው ደጀኔ, ጄ/ል

እዚያ አንቶኖቭ ውስጥ ያለው ወታደር በሙሉ በታላቅ ፌሽታ አጨበጨበ። በዚያ አንቶኖቭ ውስጥ የነበሩትና ዛሬም በሕይወት የሚገኙት ሌ/ኮ/ል ካሳዬ ታደሰ ለቢቢሲ አማርኛ እንደተናገሩት… "መንግስቱ ተገድሏል ሲባል መጀመርያ ደነገጥኩ፤ ከዚያ ሁሉም ሲያጨበጭብ እኔም ማጨብጨብ ጀመርኩ" ሲሉ የወቅቱን ድራማ ገልጸዋል፡፡

ሰማይ ላይ አንቶኖቩ ውስጥ ይህ ሲሆን የአሥመራ ሬዲዮ በበኩሉ መንግሥቱ መገደሉን አወጀ።

ከአንድ ሰዓት ተኩል በረራ በኋላ ጄኔራል ቁምላቸው ኮማንዷቸውን ይዘው አዲስ አበባ ጦር ኋይሎች ልደታ አርሚ አቪየሽን ገብተዋል። ግማሾቹን ኮማንዶዎች ደግሞ እዚያው ቦሌ አየር መንገድን እንዲቆጣጠሩ አድርገዋል። የዚህ ልዩ ኮማንዶ ተግባር ሬዲዮ ጣቢያውን መቆጣጠር፣ መከላከያ ሚኒስትር ለሚገኙት መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ደግሞ ከለላ መስጠት፤ ድንገት ‹‹ለመንጌ አንገቴን እሰጣለሁ›› የሚል ኃይል ካለ አንገቱን እንደ ዶሮ መቀንጠስ ነው።

የሚገርመው የአሥመራ ሬዲዮ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እስከወዲያኛው እንደተሰናበቱ ያወጀው ገና ረፋድ ላይ ነበር። በመሆኑም ጄኔራል ቁምላቸውም እስከመጨረሻው የሚያውቁት መንግሥቱ መገደሉን ነው። ሌ/ኮ/ል ካሳዬም ይህንኑ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ከጦላይ የመጣው ሠራዊት

መፈንቅለ መንግሥቱን ለማቅናት ከአሥመራ በጄ/ል ቁምላቸው እየተመራ አዲስ አበባ ከገባው ኃይል ሌላ ከጦላይም አንድ ሻለቃ ተንቀሳቅሷል።

ጄኔራል ውበቱ ፀጋዬ ከሴረኞቹ ጋር በስሱም ቢሆን ሳይመሳጠሩ አልቀሩም። አሁንም ድረስ በሕይወት አሉ፤ አሜሪካን አገር። ወደ አዲስ አበባ የሚላከውን ጦር አዘጋጅተው እሳቸው ከሰሜን ኮሪያ የመጣ ልኡካን ቡድንን ተቀብለው እያነጋገሩ ነበር።

ጦላይ ያለው ልዩ ኮማንዶ የቁልምጫ ስሙ ''ስፖርታ'' ይባላል። ሰሜን ኮሪያዎች ለከተማ ውጊያ፣ ለጨበጣ ፍልሚያ በልዩ ጥንቃቄ ያሰለጠኑት ጦር ነው።

ጄ/ል ውበቱ ጥርት ያለ መመርያ ባይደርሳቸውም 150 የሚሆኑትን ምርጥ ምልምሎች በወታደራዊ ሄሊኮፕተር ወደ አዲስ አበባ ላኳቸው። ፖስታ ቤት መገናኛ ሚኒስትር አካባቢ በሚገኝ ሜዳ ላይ ሆነው ትዕዛዝ እንዲጠባበቁ ተደረጉ። ኋላ ላይ 4ኛ ክፍለ ጦር...

አምባሳደር ጋ፣ ኢትዮጵያ ሆቴል ጎን፣ መከላከያ ሚኒስትር ውስጥ …

ከኢትዮጵያ ሆቴል ትይዩ በዋናው የመከላከያ ሕንፃ 1ኛ ፎቅ የጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ይገኛል። ይህ አዳራሽ ፊቱን ወደ ወርቃማው የብሔራዊ ባንክ የሰጠ ነው።

በዚህ አዳራሽ 18 መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ሴራ እየጎነጎኑ ነው። ቁጥራቸው ይጨምራል ይቀንሳል። ሆኖም በአገሪቱ አንድም የቀረ ቱባ ጄኔራል የለም።

በኢትዮጵያ የመጀመርያው አብዮታዊ ጄኔራል፣ ተወዳጁ፥ ደርባባው፣ አንደበታቸው የረጋው ጄ/ል መርዕድን ጨምሮ የባሕር ኃይል አዛዡ ሪር አድሚራል ተስፋዬ ብርሃኑ፣ የአየር ኃይል አዛዡ ጄኔራል አምሐ፣ የምድር ጦር አዛዡ ጄኔራል ኃይሉ፣ የፖሊስ ሠራዊት አዛዡ ጄኔራል ወርቁ ይገኙበታል።

ስለ ጀግንነታቸው ሳር ቅጠሉ የመሰከረላቸው እነ ጄኔራል ፋንታ በላይ፣ እነ ጄኔራል አበራ አበበ፣ እነ ጄ/ል ደምሴ ቡልቶም አሉበት። ስለነዚህ ጄኔራሎች የጦር ጀብድ እንኳን ወታደሮቻቸው አንዳንድ የሰሜን ተራሮችም አፍ አውጥተው ባይናገሩ...ማን ቀረ ታዲያ?

እርግጥ ነው ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ በአካል አምባሳደር-ብሔራዊ አካባቢ አይሁኑ እንጂ በመንፈስ አብረዋቸው ናቸው። እርሳቸው አሥመራ ትልቁን የቤት ሥራ ሠርተው ጨርሰዋል። የአገሪቱ ሁለት ሦስተኛ ጦር በርሳቸው ሥር ነው ያለው።

አሁንም ድረስ አስገራሚው ነገር ታዲያ የአሥመራ ጦር መጀመሪያ በታቀደው መሠረት የመንጌ አውሮፕላን መመታቷን ነው የሚያውቀው። ይህንኑም በሬዲዮ አስነግሯል።

እነዚህ 18 የጦር አበጋዞች ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋውን የአገሪቱን ሠራዊት ያዛሉ። ሁሉም በመፈንቅለ መንግሥቱ ጉዳይ ላይ መግባባት ደርሰዋል። ሆኖም እዚያው መከላከያ ሚኒስትር ስብሰባ ላይ ናቸው። ይህ ይሆን መዘናጋትን የፈጠረባቸው? ምን ዓይነት ምድራዊ ኃይል መጥቶ ይህን 'ኩዴታ' ሊያከሽፍ ይችላል?

ስክነት የራቃቸው ጄኔራል አበራ ብቻ ናቸው። እስራኤል ነው የተማሩት። የዘመቻ አዛዡ ጄኔራል አበራ ወትሮም ችኩል ናቸው ይባላል። ቀልባቸው የሆነ ነገር ሳይነግራቸው አልቀረም። በስብሰባው መካከል ወጣ እያሉ ግቢውን ይቃኛሉ። በዚህ መሀል የታንክ ቃቃታ የሰሙ መሰላቸው።

የመከላከያ አስተዳደር መምሪያ አዛዡን ጄኔራል ዑመርን አስከትለው የመከላከያ ግቢ የባንዲራ መስቀያው ጋ ቆመው መከላከያ ቢሮ ውስጥ ያለውን ሰው በሙሉ ወደ ግቢው እንዲሰለፍ አዘው ንግግር ማድረግ ጀመሩ፤ የመንጌን ፍጻሜም አበሰሩ። ተጨበጨበ…ቪቫ ኩዴታ ተባለ. . .

አጭር የምስል መግለጫ

መከላከያ ሚንስትሩ ጄ/ል ኃይለጊዮርጊስ ለጄ/ል ደምሴ ቡልቶ ዕውቅና እየሰጡ። ከመከላከያ ሚንስትሩ ጎን ቆመው የሚታዩት ጄ/ል አበራ ናቸው-ሟች እና ገዳይ።

የመከላከያ ሚኒስትሩ መገደል

የደኅንነት ሚኒስትሩ ተስፋዬ ወ/ሥላሴ ሴራ ሸትቷቸዋል፤ ባምቢስ ከሚገኘው የደኅንነት ቢሯቸው እየበረሩ ወደ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት ነዱ። የመንጌን ልዩ ረዳት መንግሥቱ ገመቹን ጠርተው አስቸኳይ ስብሰባ ጀመሩ። እነ ፍቅረሥላሴ ወግደረስም አሉበት። እንዲያውም ሰብሳቢው እርሳቸው ናቸው።

ምንድነው እየሆነ ያለው? እነ መርእድ ምንድነው እየዶለቱ ያሉት?

‹‹እረ በፍጹም›› አሉ ሚኒስትሩ። ሄደው እንዲያጣሩ ሐሳብ ቀረበ። በሄዱበት ይቀራሉ ያለ አልነበረም።

"ልዩ ነዳጅ መኖሩን አልደረስንበትም" የማዕድን፣ የፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር

ሚኒስትሩ ቁልቁል ወደ አምባሳደር በረሩ። ወደ ቢሯቸው ገብተው ወጡ።

ጄ/ል ኃብተጊዮርጊስ ወትሮም ከጄ/ል አበራ ጋር እስተዚህም ናቸው። እረ እንዲያውም ዐይንና ናጫ...። ጄ/ል አበራ የሆነ የቀፈፋቸው ነገር ያለ ይመስላል። ጄ/ል መርዕድ ከሚመሩት ስብሰባ በየመሀሉ እየወጡ ኮሪደሩን፣ አካባቢውን ይቃኙና ይመለሳሉ።

ድንገት ለቅኝት ደረጃውን ሲወርዱ፣ መከላከያ ሚኒስትሩ ደግሞ ደረጃውን ሲወጡ ተገጣጠሙ።

"አበራ! ምንድነው እኔ የማላውቀው ስብሰባ?" ሳይሉ አልቀሩም። አንዱ ሁለት ተባብለውም ሊሆን ይችላል። ብቻ ጄኔራል አበራ በቅልጥፍና ሽጉጣቸውን አውጥተው መከላከያ ሚኒስትሩ ላይ አከታትለው ተኮሱ።

ጦር ኃይሎች ቢወሰዱም አልተረፉም።

መከላከያ ሚንስትሩን ጄኔራል ኃብተጊዮርጊስን ጠርተው፣ ለመሆኑ በቢሮህ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ታውቃለህ? ብለው ጠየቁ።

ተስፋዬ ወ/ሥላሴ, የደኅንነት ሚኒስትሩ

ጄኔራል አበራ እንዴት አመለጡ? ለምን አመለጡ ?

ይህ ሁሉ ሲሆን ከአሥመራ የመጣው የጄኔራል ቁምላቸው ሠራዊት ጦር ኃይሎች ግቢ ሆኖ በተጠንቀቅ ትእዛዝ ይጠባበቃል። እንዲያውም ስልክ ወደ ጄ/ል አበራ ደውሎ አልተነሳለትም። ከጦላይ የመጣውና በሰሜን ኮሪያዎች የሰለጠነው የስፓርታ ጦርም ፖስታ ቤት አካባቢ ሥራ ፈትቶ ሜዳ ላይ ተቀምጧል። ።

ሁሉም ታዲያ ሪፖርት የሚያደርጉትም ትእዛዝ የሚቀበሉትም ከጄኔራል አበራ ብቻ ነው። የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ እሳቸው ናቸዋ።

ጄ/ል አበራ ግን ያልተጠበቀ ነገር ፈጽመው ችግር ውስጥ ገብተዋል። መከላከያ ሚኒስትሩን ከገደሉ በኋላ ወደ ቢሮ አልተመለሱም። ልዩ ኮማንዶነት የሰለጠኑት ጄ/ሉ በአጥር ዘለው አምልጠዋል።

አንዳንዶች ከጎን የሚገኘው ቡና ገበያ ግቢ ገብተው ዘበኛ ማርከው የወታደር ልብሳቸውን አውልቀው የዘበኛ ልብስ ለብሰው ተሰወሩ ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ የለም ከመከላከያ የወጡት በአጥር ሳይሆን በበር ነው፤ የአንድ ሠራተኛ ልብስ ቀይረው ነው ይላሉ።

የጄ/ል አበራ ከመከላከያ መሰወር ነገሮችን አመሰቃቀለ።

ከጦላይና ከአሥመራ የመጣው ኃይል ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ ገብቶት እርሳቸውን ይፈልጋል። እርሳቸው ግን ስልክ አያነሱም። ቢሮም የሉም። በዚያ ዘመን ሞባይል የሚባል ነገር አይታወቅ ነገር…

ጄኔራሎቹ ራሳቸውን ለምን አጠፉ?

ግንቦት ስምንት ቀትር ስምንት ሰዓት ግድም የጀመረው መፈንቅለ መንግሥት ራሱን በራሱ እየተበተበ አንድም ፋይዳ ያለው ነገር ሳያከናውን መሸበት። ደኅንነቱ ተስፋዬ ወ/ሥላሴ ሻምበል መንግሥቱ ገመቹን ይዘው መከላከያን አስከበቡ፤ ለዚያውም በታንክና በብረት ለበስ።

ከዚያ በፊት ግን ነገሩን በሰላም እንጨርሰው በሚል ሽማግሌ ተልኳል፤ ሌ/ኮ አዲስ ተድላና ኮ/ል ደበላ ዲንሳ ነበሩ አደራዳሪዎቹ።

‹‹መፈንቅለ መንግሥቱ ያበቃለት ጉዳይ ነው፤ ምንም ድርድር ብሎ ነገር የለም። ባይሆን አግዙን›› ሳይሏቸው አይቀርም፣ እነ ጄ/ል መርዕድ።

ዞሮ ዞሮ ሰዓቱ ነጎደ። ማስታወቂያ ሚኒስትር አልተያዘ፣ ሬዲዮ ጣቢያ አልተያዘ፣ ቴሌ አልተያዘ…ሰዓቱ ነጎደ። የሳር ቅጠሉ አዛዦች በሙሉ እዚያ መሆናቸው ሳያዘናጋቸው አልቀረም። የጄ/ል አበራ ድንገት ሰው ገድሎ መሰወር ግን ነገሮችን አወሳሰበ።

የመንጌ ቀኝ እጅ ሞክሼያቸው መንግሥቱ ገመቹ የልዩ ብርጌድ ኃይላቸውን ከ4ኪሎ አንቀሳቀሱ። በሂልተን አድርገው አምባሳደር ጋ ሲደርሱ 'መከላከያ ሚኒስትሩን ክበብ' አሉ።

ውስጥ እነ ጄ/ል ፋንታ በላይ፣ አነ ጄ/ል አመሃ፣ እነ ጄ/ል መርዕድ…ምን እያደረጉ እንዳሉ የሚያውቅ ምድራዊ ኃይል የለም። ሆኖም በዚያ ሰዓት መከበባቸውን እንደተረዱ ከአሥመራ ይመጣል የተባለው ኃይል ባለመድረሱ ተስፋ ቆርጠው ሊሆን ይችላል። ብቻ ጄ/ር መርዕድና ጄ/ል አመሐ ዛሬም ድረስ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ እዚያው ራሳቸውን አጠፉ።

ድኅረ ታሪክ

ግንቦት 9 ማታ ኮ/ል መንግሥቱ ከምሥራቅ ጀርመን ጉብኝታቸውን አቋርጠው ኮሽታ ሳያሰሙ ተመለሱ።

ግንቦት 10፣ ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ በገዛ ወታደሮቻቸው ተገደሉ፤ ከእርሳቸው ጋር በድምሩ 18 ከፍተኛ መኮንኖች ተመሳሳይ ክፉ እጣ ገጠማቸው። በሟቾቹ ሬሳ ላይ እጅግ የሚቀፍ፣ ታሪክ የሚጸየፈው የሰይጣን ድርጊት ተፈጸመ።

ከሦስት ቀን በኋላ ጄኔራል ፋንታ በላይ ከተደበቁበት ኮንቴይነር ወጡ። ለጥቂት ወራት ማዕከላዊ ለብቻቸው ተነጥለው ታስረው ሳሉ እስከዛሬም ይፋ ባልሆነ ሁኔታ "ጠባቂያቸውን ገድለው ሊያመልጡ ሲሉ ተገደሉ" ተባለ።

በሦስተኛው ሳምንት መከላከያ ሚኒስትሩን ገድለው ያመለጡት ጄ/ል አበራ ጉለሌ አካባቢ ከተደበቁበት ዘመድ ቤት ተከበቡ። በመስኮት ዘለው ጣሪያ ላይ ወጥተው ሊያመልጡ ሲሉ በአንድ ወጣት ፖሊስ ግንባራቸውን ተመትተው ወደቁ። አንዳንድ የሰው መረጃዎች ጄ/ል አበራን አሳልፎ የሰጣቸው ዘመድ ዛሬም ድረስ በጸጸት ይኖራል ይላሉ።

ከሆኑ ወራት በኋላ የአሥመራውን አየር ወለድ ጦር አዲስ አበባ ይዘው የመጡት ጄኔራል ቁምላቸው በአንዳች ተአምር አምልጠው አሜሪካ ገቡ ተባለ። ሲአይኤ እንዳሾለካቸው ተጠረጠረ።

ከዓመት በኋላ ግንቦት 13፣ 1981 መፈንቅለ መንግሥቱ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ 12 ጄኔራሎች ድንገት ለውሳኔ ተጠሩ። የወታደራዊ ፍርድ ቤት የመሀል ዳኛው ጄ/ል አሥራት ብሩ በብጣሽ ወረቀት የተጻፈችና ከኮ/ል መንግሥቱ እንደተላከች የምትገመት አንዲት ወረቀት እንባ እየተናነቃቸው አነበቧት ተባለ። በ12ቱ ላይ ሞት ተፈረደ። ፍርደኞቹም እንዲህ እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ‹‹ቤተሰባችንን ሳንሰናበት አትግደሉን…››፣ ‹‹ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ዕድሜ የለውም››፣ ‹‹ልጆቻችንን አደራ››። ያንኑ ምሽት ተረሸኑ።

ከስዒረ መንግሥት ሙከራው ከ2 ዓመት በኋላ ግንቦት 13 ቀን ኮ/ል መንግሥቱ ከአገር ሸሹ።

የኮ/ሉን ሽሽት ተከትሎ ለአንድ ሳምንት ርዕሰ ብሔር የሆኑት ጄ/ል ተስፋዬ ገብረኪዳን ሞታቸውን እየተጠባበቁ ለነበሩ ጥቂት የመፈንቅለ መንግሥቱ ተከሳሾች ምሕረትን አወጁ።

ከቢቢሲ አማርኛ የተወሰደ
Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”