ኤርትራ ሆይ ...("ዳቦ ለጠየቀ ድንጋይ") - ታሪኩ ደሳለኝ /ሚኪ/

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
selam sew
Leader
Leader
Posts: 599
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

ኤርትራ ሆይ ...("ዳቦ ለጠየቀ ድንጋይ") - ታሪኩ ደሳለኝ /ሚኪ/

Unread post by selam sew » 16 Jul 2018 13:22

ኤርትራ ሆይ ...
("ዳቦ ለጠየቀ ድንጋይ")

አርብ ወደ ማታ የእጅ ስልኬ ደጋግማ "የመልስ ያለህ…" ጩኸቷን ስታሰማ
"ሃሉ" አልኩኝ፤
"አርቲስት ታሪኩ ደሳለኝ ነህ?" ሲል ጠየቀኝ ድምፁ የጓልማሳ ሰው የሚመስለው ደዋይ።
"አዎ ታሪኩ ነኝ" እያመነታው አረጋገጥኩለት።
"ከብሔራዊ ቲያትር ቤት ነው የደወልነው" ፣ ሰዓቴን ተመለከትኩ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ33 ደቂቃ ይላል። በዚህ ምሽት ይህ አንጋፋ ቲያትር ቤት በምን ምክንያት እኔ ጋር ይደውላል? የሚል ጥያቄ ሽው ቢልብኝም፣ ደዋዩ ንግግሩን ቀጠለ
"ነገ ቅዳሜ ከጠዋቱ 1 ሰዓት ብሔራዊ ቲያትር ቤት በመገኝት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ለመቀበል እና እሁድ ሚሊኒያም አዳራሽ በሚኖረው ዝግጅት ላይ ለመግባት የሚያስችልህን ባጅ እንድትወስድ ልንነግርህ ነው" አለና ከግራ መጋባት ገላገለኝ።
"ይቅርታ ወንድሜ የመገኘት ፍላጎቱ ስለሌለኝ ነው አመሰግናለሁ" ስል በትህትና መለስኩለት። ከጥቂት ሰኮንዶች ዝምታ በኋላ ንግግሩን ቀጠለ
"ባጁ እኮ ኤርፖርት ውስጥ ጭምር ነው የሚያስገባህ ?! እንዲሁም የእሁዱ ኮንሰርት ላይም ተገኝበታለህ" ሲል ማጓጓት ባጀበው ድመፁ ሊያባብለኝ ሞከረ።
"ያለከው ገብቶኛል፣ ግን መምጣት ስለማልፈልግ ነው" ስል ፈርጠም ብዬ አቋሜን ደገምኩለት። ይህ ምላሼም የመጨረሻ ሆኖ ከቲያትር ቤቱ ደዋይ ጋር የነበረኝ ምልልስ ተቋጨ።
…ስልኬን እንደዘጋው በድንገቴ ሃሳበ እመናተል ጀመር። አዎን! ልክነኝ!!! ኢሳያስ አፈወርቂ የተባለ መርዘኛ፣ የበላበትን ውጭት ሰባሪን በክብር አልቀበልም። በሱ ስም በተሰናዳው የሙዚቃ ዝግጅት ላይም ታድሜ እየፈነጠዝኩ "አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሀገር" ብለው ታሪካዊ ሰማዕትነትን በክብር የተቀበሉ ታላላቆቼን አፅም አላሳዝንም። ለደቂቃዎች ያህል ቁጭትና ንዴት በደም ስሬ ተራወጠ።
…ብስጭትጭት ብልም ግን ቀይ ባሕርን ታካ የተዋበችውን የእናት ምድሬን ክፋይ ኤርትራን ጠልቼ አይደለም። የሻዕቢያውን ኢሳያስ እና ሴረኛ ካቢኔዎቹን ነፍሴ ተፀይፋ እንጂ። የአባቶቻቸውን ሕልም አጨንግፈው ሀገር በመገንጠላቸው እንጂ። ለጎሳ ፖለቲካ የክብር ስፖንሰር በመሆናቸው እንጂ…
መቼም ሰሞኑን በሃፍረት አንገት የሚያስደፉን ጉዶቹ እንደ ችግኝ ተፈልፍለዋል። ከአዱ—ገነት ወደ ደቡብ ፊታችንን ስንመልስ፣ ዕለቱኑ የኢንዱስትሪ ፓርክን ለመጎብኘት በሚል ወዲ አፈወርቂን አዋሳ እናገኘዋለን። የእራት ግብዣው መድረክ አስተዋዋቂ ግሩም ጫላ የተባለ መደዴ—የድል አጥቢያ አርበኛ (በሚሊኒየም አዳራሽ በነበረው ፕሮግራምም በታላቁ ቴዲ አፍሮ ላይ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ አይነት ተንኮል ሲፈፅም ታዝቤዋለሁ) የወንበዴዎች ዋነኛ አለቃ የነበረውን ኢሳያስ አፈወርቂን ሲያስተዋውቅ የአፋቤት አንበሳ፣ የናቅፋ ተራራ ነብር፣ ጥላቱን የደመሰሰ አይበገሬ ታጋይ፣ ነጻነቱን ከጨቋኞች የነጠቀ ጀግና… እያለ ከማቆለጳጰስም በዘለለ የአባቶቹን፣ የአጎቶቹን፣ የወንድሞቹን፣ የወገኖቹን… በኤርትራ ምድር የተፈፀመ ታላቅ ተጋድሎን ሲያራክስ፣ ናቅፋ ተራራ ላይ ወደር በማይገኝለት ጀግንነት ለክቡድ ዓላማ የወደቁትን የኢትዮጵያ ቁርጥ ቀን ልጆች አፅም ሲወቅስ አምሽቷል። እንኳንም ገደልካቸው፣ እሰይ እንኳን ቀበርካቸው፣ እልልታ ለግንጠላህ… እያለ በአስካሪስነት ለኢሳያስ አሸረገድኩ ብሎ የአርበኝነትን አእምድ ሲያፈራርስ አምሽቷል።
እውነት እውነት እላችኋለሁ:— በዚህች በኢትዮጵያ ምድር ይህን ሲባል መስማት እጅጉን ያሳፍራል! ያስደነግጣል! አንገት ያስደፋል! በጥፍር እስከ መደበቅ ያሸማቅቃል።
አረ ለመሆኑ:— የማን አባት? የማን ልጅ? የማን ባል? የማን ሚስት? የማን ወንድም ነው? በኤርትራ ተራሮች ደመ—ከልብ ሆኖ የቀረው? የቀይ ባሕር አሳ ነባሪስ ቀለብ ሆኖ ያለፈው ማነው? እኮ ማነው ለእናት ሀገሩ ብሎ ፔትሮ ዶላር ካሰከራቸው ገንጣይ አስገንጣይ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ የወደቀው? …የነዚህ ሰዎች ቤተሰቦችስ ዛሬ አባቶቻቸው፣ ልጆቻቸው፣ ወንድሞቻቸው እህቶቻቸው ጠላት መባላቸውን ሲሰሙ ምን ይሰማቸው ይሆን?
ዋለልኝን አሳስቶ፣ ኦነግን በሞጋሳ አሳድጎ፣ ህወሓትን ወልዶ፣ ግብፅን ለማስደሰት፣ ሳውዲን ለማስፈንደቅ… ኢትዮጵያን ሁለት ያደረገው "ኢሱ" ይህንን ሲሰማ በልቡ ምን ይለን ይሆን?!
መቼም ይህ ንግግር በእንጭጩ "አስተዋዋቂ" ብቻ የተዘጋጀ ነው ብለን የምናልፈው ተራ ጉዳይ አይደለም። ይህም ሆኖ ዛሬ ለሀገራዊው ለውጥ ብለን ስህተቱን በዝምታ ብናልፍም ነገሩን ተውነው ማለት እንዳልሆነ ግን መታወቅ አለበት። ቆሽታችን አልተላጠምም ማለት አይደለም።
በተረፈ የአንድ እናት ልጆች የነበሩ ህዝቦች አንድ እንዲሆኑ ምኞቴ የምር ነው። እኔም አስመራ፣ ምጽዋ፣ ናቅፋ ተራሮችን… እንዲሁ ሳላውቃቸው አብዝተው ይናፍቁኛል። የመጎብኘት ጉጉቴም ጣራ የነካ ነው። አንዲት ኢትዮጵያን ያሉ ታላላቆቼ ደም የተቀላቀለበት ቀይ ባሕር ላይ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጥ እፈልጋለሁ። አጥንታቸው በተሰባበረበት ተራራ ላይ የህሊና ፀሎት ማድረግ እፈልጋለሁ። ከአባቶቼ የተጋድሎ መንፈስ ጋር የመውራት፣ የመገናኘት፣ በሀገር ፍቅር የመባረክን ዕድል አብዝቼ እሻለሁ።
የራስ አሉል ጦር የተወረወረበት—ዶጋሌን፣ ዘራዓይ ደረስ የተወለደበትን መንደር፣ በ1934 ዓም ተምስርቶ የነበረውን "የአንድነት የሀገር ፍቅር ማህበር" ቢሮን፣ ሻዕቢያ የተፀነሰበትን ቃኘው
ስቴሽን፣ እነ ጆነራል ደምሴ ቡልቶ ከምርጡ ሠራዊታችን ጋር የወደቁበትን፣ ዝነኛው ባሕር ኃይላችን ተመስርቶ የፈረሰበትን፣ የቀይ ኮከብ ዘመቻ አሻራዎችን… የማየት ብርቱ ምኞት እንደሚያንገበግበኝ አልሸሽግም።
እስከዚያው ግን ብርቱው ጠ/ሚ አክሊሉ ሀብተወልድ የኢትዬጵያ እና ኤርትራን አንድ አገርነት ክዶ ፈርደ ገምድል በሆነው የተባበሩት መንግስታት ላይ ያሰሙትን ምሬት፣ ለሰሞነኛው ሽንፈታችን መቆዘሚያ እደርገዋለሁ:— "ዳቦ ለጠየቀ ድንጋይ!"
ክብር ለቀድሞ ሠራዊት!!!

ታሪኩ ደሳለኝ /ሚኪ/
ሐምሌ 9/2010
አዲስ አበባ

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”