የወታደሮቻችን ነገር ከዲ/ን ዳንኤል ክብረት

ግጥሞች፣ታሪኮች፣ፎቶዎች፣ሙዚቃዎች
Poems,Short stories, graphics,pictures,musics,Technology
selam sew
Leader
Leader
Posts: 616
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

የወታደሮቻችን ነገር ከዲ/ን ዳንኤል ክብረት

Unread post by selam sew » 21 Dec 2015 23:25

የወታደሮቻችን ነገር ከዲ/ን ዳንኤል ክብረት

የመቅደላው ጀግና ዐፄ ቴዎድሮስ በመጨረሻዋ ሰዓት ለጄኔራል ናፒየሪ በጻፉት ደብዳቤ አበክረው የጠየቁት ነገር ከሁለት ቀናት በፊት በተደረገው ውጊያ የወደቀውን የወዳጃቸውንና የጦር መሪያቸውን የፊታውራሪ ገብርዬን አስከሬን ለመቅበር እንዲፈቀድላቸው ነበር፡፡ ‹‹ፊታውራ ገብርዬን የኔን ወዳጅ ሳላነሣው ያደርኩ ከሞትኩኝ ሁሉንም አብረው ይቅበሩኝ ብየ ነበር፡፡ ቁሜ ከዋልኩ ግን ልቅበረው ይፍቀዱልኝ›› ይላል ደብዳቤው፡፡ ለሀገሩና ለወገኑ በክብር የተሠዋ አስከሬኑም የክብር ዕረፍት ይሻዋልና፡፡
አሜሪካኖችና አውሮፓውያን የተሰጣቸውን ግዳጅ ለመወጣት የዘመቱ ወታደሮቻቸው ሲሠው በክብር አስከሬናቸውን ወደ ሀገር በማምጣት በብሔራዊ ሥነ ሥርዓት የመቅበር ያልጠፋ ልማድ እንዳላቸው በየጊዜው ሚዲያው ያሳየናል፡፡ እነዚህ ወታደሮች ሀገራዊ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የዘመቱ በመሆኑ መሥዋዕትነታቸውም ሀገራዊ ሆኖ መታሰብ አለበት፡፡
በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመን ታሪክ የተሠዉ ወታደሮችን በክብር የመዘከር፣ በክብር የመቀበልና በክብር የመቅበር ሥነ ሥርዓት አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ በኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት የተሠዉ ስንት ወታደሮች ናቸው? የተሠዉትስ ወታደሮች መርዶ እንዴት ተነገረ? የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውስ እንዴት ተከናወነ? ሚዲያውስ ለዚያ ምን ዓይነት ሽፋን ሰጠው? የሁል ጊዜ ጥያቄዬ ነው፡፡ እኔ ሳልሰማና ሳላውቅ ተከናውኖ ካልሆነ በቀር፡፡ ለምንስ አስከሬናቸው በወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ታጅቦ፣ ሰንደቅ ዓላማ ለብሶ፣ ብሔራዊ መዝሙር እየተዘመረ፣ ሕዝቡ ወደ አደባባይ በነቂስ ወጥቶ አላከበርናቸውም? እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በአፍሪካ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች ዘምቷል፡፡ ሲዘምትም በክብር እንደተሸኘ በሚዲያዎቻችን አይተናል፡፡ እነዚህ ዘማቾች ሁሉም በሰላም ነው የተመለሱት? የተሠዋ ካለ ለምን ይፋዊ በሆነ ሀገራዊ ሥነ ሥርዓት አስከሬኑን ተቀብለን አልቀበርነውም? ፖለቲካው ተፈርቶ ከሆነ ለግዳጅ የተሠማራ ወታደር ወይ በድል መመለስ፣ ወይ መማረክ፣ ወይ መቁሰል አለያም መሠዋት እንደሚያጋጥመው እንኳን እኛ ታሪካችን በጦርነት የተሞላው ቀርቶ ሌሎችም ያውቁታል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሶማልያ ሲዘምቱ ፓርላማው ወስኖ ነው የዘመቱት፡፡ የሄዱት በእር በርስ ጦርነት ሲታመስ ወደኖረውና እጅግ አስቸጋሪ ወደሆነው የጦርነት ሥፍራ ነው፡፡ ከሶማልያ መንግሥት ወታደሮችና ከአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ጦር ጋር በጋራ በመሆን በሶማልያ ከአልሸባብና ከሌሎችም ኃይሎች ጋር በመዋጋት ያገኙትን ድል ሚዲያዎቻችን ይዘግባሉ፡፡ መቼም የሄዱት ለጦርነት ነውና፣ በጦርነት ውስጥ መግደል፣ ድል ማድረግና መማረክ እንዳለ ሁሉ መሞት፣ መቁሰልና መማረክም አለ፡፡
ታድያ የሀገሬ ወታደሮች አልተሠዉም፣ አልቆሰሉም፣ አልተማረኩም? የሄዱት ሁሉ ሰላም ናቸው? ከሆኑ መልካም፡፡ ግን ቦታውም የነ አልሸባብ ቦታ፣ ሁኔታውም ጦርነት፣ ሰዎቹም ወታደሮች ናቸውና ቢያንስ መሞትና መቁሰል አይቀርም፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ ሚዲያዎች በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅና በሶርያ ጦርነት የተሠዉትንና የቆሰሉትን ማንነት እንደሚናገሩት፣ በክብርም ሲቀበሩ እንደሚያሳዩት፣ የኛዎቹ የተሠዉት በክብር ሲቀበሩ፣ የቆሰሉት በክብር ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ለምን እንደ ሕዝብ አናያቸውም? ለመሆኑስ በክብር የተሠዉ የኢትዮጵያ ወታደሮች መቃብር የት ነው?
ወደኋላም ተመልሰን ከአድዋ ጦርነት በኋላ የሆነውን ስናስታውስ በእንዳ ኢየሱስ ያለው የአባቶቻችንን መቃብርና ከዚያ እልፍ ብሎ የሚገኘውን የጣልያኖች መቃብር መመልከቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ በእንዳ ኢየሱስ የሚገኘው የአድዋ ዘማቾች አባቶቻችን መቃብር ለመሥዋዕትነታቸው የማይመጥን ነው፡፡ አልፎ አልፎም ፈርሶ እናየዋለን፡፡ የጣልያኖቹ መቃብር ግን በክብር ታጥሯል፡፡ ጠባቂም ተመድቦለታል፡፡ መቃብሩንም ለማየት የጣልያን ኢምባሲ ፈቃድ ይጠይቃል፡፡
በአሥራ ሰባቱ የደርግ ዓመታት የዘመቱት ወታደሮች ኢትዮጵያ የመለመለቻቸው፣ ያሠለጠነቻቸውና ያዘመተቻቸው ነበሩ፡፡ ምንም ጦርነቱ የእርስ በርስ ጦርነት ቢሆንም፡፡ የተሠዉት አብዛኞቹ ወታደሮች ለቤተሰብ መርዶ አልተነገረም፡፡ በተለይ ኤርትራ በረሃ የቀሩት መጨረሻቸው ምን እንደሆነ አልታወቀም፡፡ ጦሩ ሲበተን ወደ ቤተሰባቸው መምጣት የቻሉት ቁርጣቸው ታወቀ፤ ከዚያ ውጭ ያሉት ግን አሁንም ለቤተሰብና ለሀገር ጥያቄ እንደሆኑ ናቸው፡፡
የአንድ ወታደር ክብር የሀገራዊ ዓላማና የሀገራዊ ግዳጅ ክብር ማሳያ ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ በአውሮፕላን በተጓዝኩ ቁጥር ለአሜሪካ ወታደሮች የሚሰጠውን ክብር አደንቃለሁ፡፡ አውሮፕላኑ ምድር ደርሶ ተሣፋሪዎቹ እንደተቀመጥን ለወታደሮቹ ቅድሚያ ተሰጥቶ እያጨበጨብን ወደ በሩ እንሸኛቸዋለን፡፡ ወደ አውሮፕላን ውስጥ ስንገባም አስተናጋጆቹ ‹ዩኒፎርም የለበሱ ጀግኖቻችን አሉና እናክብራቸው›› ብለው ያውጃሉ፡፡ ሁላችንም እንጨበጭባለን፡፡ እኔ የሀገሬ ወታደር በአውሮፕላን እንኳን ባይሆን በታክሲና በአውቶቡስ፣ በመዝናኛ ቦታዎችና በአገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲህ ሲከብር ማየት እናፍቃለሁ፡፡
ወታደሮቻችንን ጉሮ ወሸባየ ብለን እንደሸኘናቸው ሁሉ የጀግና አቀባበል እንድናደርግላቸው፣ ሲሠዉ በክብር አደባባይ ወጥተንና የሞቱለትን ሰንደቅ ዓላማ አልብሰን እንድንሸኛቸው፣ የቆሰሉትን በክብር እንድንቀበላቸው፣ ያስገኙት ድል ብቻ ሳይሆን የገጠማቸው ፈተናና የከፈሉት መሥዋዕትነትም እንዲነገርላቸው እመኛለሁ፡፡ የክብር አቀባበልን ላሸነፈ ሯጭና እግር ኳስ ተጨዋች፤ የክብር አቀባበርንም ለአርቲስት ብቻ ማን ሰጠ?

ተዛማጅ ጽሁፎች

Post Reply

Return to “Ethio Art and Culture..ኢትዮ ጥበብ ፤ስነ ጽሁፍ ፤”