(ስሜነህ ጌታነህ)
« ክፍል አንድ»

አሁን የማወራችሁ ስለ ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ነው። ቴሌ ፕሪንተርን የ ዛሬ 50 አመት ሰርተው በዛን ጊዜ ፓተንት የወሰዱ ናቸው ። በአለም አቀፉ የቴሌኮሚኒኬሽን. ህብረት ውስጥ ለ 40 አመት በትልቅ ሃላፊነ ት ሰርተዋል ። ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጋር አንድ ታሪክ አላቸው። ሰውየው የሀገር ባለውለታና ዛሬም ደከመኝ የማይሉ ናቸውና ታሪካቸውን ብታነቡትስ ።
አንድ ቀን ኢንጂኒየር ስልክ ደውለውልኝ “ለምን አንኮበር ደረስ ብለን አንመለስም?” አሉኝ፡፡ አንኮበር ስለሚገኘው ሎጃቸውና የምኒልክ ቤተመንግስት አጫውተውኝ ነበርና ያንኑ እንድጎበኝ ፈልገዋል፡፡ “ታሪክ የማወቅ ጉጉቴን የተረዱ ታላቅ ሰው” ስል አመስግኜ ወደ አንኮበር ለመሄድ ራሴን አዘጋጀሁ፤ ጓዜን አሰናዳሁ፡፡ በቀጠሮአችን ተገናኝተን ወደ ቦታው ስናመራ በበርካታ ጉዳዮች ላይ እየተጫወትን፤ ሃሳብ እያነሳንና እየጣልን አንኮበር ደረስን፡፡
ማስታወሻ በአንኮበር
የአጼ ምኒልክ ቤተመንግስት በ1936 ዓ.ም በጣሊያኖች ሲቃጠል ኢንጂኒየር የሰባተኛ ዓመት እድሜያቸውን እያከበሩ ነበር፡፡ እናም የልጅነት ቁጭታቸውን ሊወጡ አስበው የአንኮበር ሎጅን ለመመስረት ወገባቸውን ታጥቀው ተነሱ፡፡ ኢንጂኒየር ከሰባት ዓመታት በፊት የአንኮበር ሎጅን ሲመሰርቱ ውስጣቸው በትልቅ እርካታ ተሞላ፡፡
እስከዛሬ አርባ ፎቅ በደረጃ መውጣቴን አላስታውስም፡፡ አንኮበር ቤተመንግስት የተሠራው ከፍታ ቦታ ላይ ስለሆነ ሽቅብ የሚደረገው ጉዞ ቢሰላ በግምት ግን ወደላይ አርባ ፎቅ ይሆናል፡፡ አርባውን ፎቅ እንደጨረስን ነው ቤተመንግስቱን የምናገኘው፡፡ በትንሹ ወደ ፎቁ ለመውጣት 25 ደቂቃ ይወስዳል፡፡ ከቀኑ ስድሰት ሰአት ተኩል ላይ ሎጁ ጋር እንደደረስን መጠነኛ እረፍት ወስጄ የኢንጂኒየርን ያልነጠፈ ወግ በተመስጦ ማድመጥ ቀጠልኩ፡፡ “ስለእኚህ ሰው ምን አስተዋልክ?” ብትሉኝ፤ ስክን ያለ ሰብእናቸውን ነው፡፡ ቶሎ አይደሰቱም፤ በቶሎ አይናደዱም፡፡ ቸኩለው ሃሳብ አይሰነዝሩም፡፡ ቆም ብለው አሰብ ሲያደርጉ በርጋታ ይሞላሉ፡፡
ቴሌ ፕሪንተርን ለሀገራችን ያስተዋወቁ
በወቅቱ የአማርኛ ቴሌፕሪንተሩን ሲሰሩ 32ኛ ዓመታቸውን ያከበሩት ኢንጂኒየር ተረፈ ራስወርቅ ይህን ቴክኖሎጂ በማስተዋወቃቸው ልዩ አድናቆትን አትርፈዋል፡፡ ተወዳጁ ደራሲና ጋዜጠኛ በአሉ ግርማ የዛሬ 46 ዓመት በመነን የእንግሊዝኛ መጽሔት ላይ ቴሌ ፕሪንተር ስለሰሩት ኢንጂነር ፣ አስደናቂ በሆነው ችሎታው “…የራስዋ ፊደል ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በወጣት መሃንዲስ አማካኝነት፣ የአማርኛ ቴሌፕሪንተር ባለቤት ሆነች” ሲል አብስሮ ነበር፡፡ በሙያቸው ለአስር ዓመታት በሀገራቸው ያገለገሉት ኢንጂኒየሩ፣ ቴሌፕሪንተሩን በሰሩ ማግስት የዓለም አቀፉ የቴሌኮምኒኬሽን ህብረት ባልደረባ ለመሆን በቁ፡፡ በህብረቱ መቀመጫ ስዊዘርላንድ አገር ለአርባ ዓመታት ከማገልገላቸውም በላይ የጎለበተ ልምድ አካብተዋል፤ ልምዳቸውንም አካፍለዋል፤ ልጆቻቸውንም ወልደው አሳድገዋል:: ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ዓለም አቀፉን የቴሌኮምኒኬሽንን ህብረት በሃላፊነት በማገልገል ኢንጂኒየር የመጀመሪያው ናቸው፡፡ ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡
ኢንጂኒየር ሲታዩ የ79 ዓመት አዛውንት አይመስሉም፡፡ “ጠንካራ ነዎት!” ስላቸው ዘወትር የአካል ማጎልበቻ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንደረዳቸው ነገሩኝ፡፡ በተለይ የሌሊቱ ሰዓት ለስፖርት ምቹ ጊዜ እንደሆነላቸው ጠቆም አደረጉኝ፡፡ ቀኑንማ ዛሬም በጡረታ እድሜያቸው በሥራ ነው የሚያሳልፉት፡፡
ትውልዳቸው ሰሜን ሸዋ፤ አንኮበር ነው፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት ቤት እንደደረሰ በትውልድ ቀዬአቸው ፊደል ከቆጠሩ በኋላ የአስር አመት እድሜ ሲሞላቸው (የዛሬ 69 ዓመት መሆኑ ነው) ወደ አዲስ አበባ መጥተው በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡ ያኔ የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ቤት ታሪክ፤ ተፈሪ መኮንን የሰማንያ ስምንት ዓመት እድሜ ጠገብ አንጋፋ የትምህርት ተቋም ነው፡፡ ኢንጂኒየርም በትምህርት ቤቱ እንደ ማለፋቸው ብዙ ትዝታ አላቸው፡፡
ታዳጊው ተረፈ በልጅነታቸው እርሻ ለመማር ነበር ያሰቡት፡፡ ግና አንድ ሚስተር ዳሮ የሚባል አስተማሪያቸው የእርሻ ትምህርት እንደማይሆናቸው ሲመክራቸው የሳይንሰ ትምህርትን ምርጫቸው አደረጉ፡፡ አዛውንቱ ኢንጂኒየር “እስከ ዛሬ ይህን ሰው አመሰግነዋለሁ” ይላሉ፡፡ ኢንጂነር ከተፈሪ መኮንን አስራ ሁለተኛ ክፍልን እንደጨረሱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን ተቀላቀሉ፡፡ በዚያን ዘመን በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት የትምህርት መምረጫ ጊዜ ነበርና የሳይንስ ትምህርት ምርጫቸውን የኤሌክትሪክ መሃንዲስ ትምህርትን ተያያዙት፡፡
አገር ቤት ለሁለት ዓመታት ከተማሩ በኋላ፣ ወደ አሜሪካ አገር በመሄድ በኤሌክትሪክ ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለማግኘት በቅተዋል፡፡ ኢንጂኒየር አሜሪካ የተማሩት ትምህርት ቤት፤ በ1824 በተቋቋመውና ሮይ ኒዮርክ ክፍለ ግዛት ውስጥ በሚገኘው በመጀመሪያው የአሜሪካ የቴክኒክ ትምህርት ቤት - ሬንስለር ፖሊቴክኒክ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ የግል ቢሆንም ኢንጂኒየር ባገኙት የነጻ ትምህርት እድል በማግኘት ነበር ወደዚያው ያቀኑት፡፡ የሁለተኛ ዓመት የአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪ ተረፈ ራስወርቅ፤ ሬንስለር ፖሊቴክኒክ ሲደርሱ ከሶስተኛ አመት ተማሪዎች ጋር ነበር ትምህርታቸውን የቀጠሉት፡፡ በኢንጂኒየር ተረፈ እምነት ትልቁ የመሃንዲስነት ትምህርት አእምሮን ማሰራት ነው፡፡ አንጎልን ማስፋት ነው፡፡“አንጎልን ካሰለጠነው ብዙ ማሰብ እንደሚችል ተምረናል” ይላሉ ኢንጂነር፡፡ የተማሩበት ትምህርት ቤት ዓላማ ተማሪዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ ነው፡፡ እርሳቸውም ትምህርት ቤቱ በእጅጉ እንደጠቀማቸውና ያምናሉ፡፡ ውስጣቸው ያለውን አቅምም አውጥተው እንደተጠቀሙበት ያምናሉ፡፡
ኢንጂኒየር ተረፈም ሀገሬን በሙያዬ ላገለግል እችላለሁ ብለው ስለሚያምኑ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ አገር ቤት የመመለስ ውጥን ነበራቸው፡፡ በ1953 ዓ.ም ትምህርታቸውን አጠናቀው ከባህር ማዶ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የተደረገላቸውን አቀባበል በልዩ የደስታ ስሜት ነው የሚገልጹት፡፡ አቀባበሉ በልዩ ማእረግ ነበር፤ እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ነበር በልዩ ክብር እንዲያርፉ የተደረገው፡፡
በወቅቱ ሥራ አማርጠው እንዲጀምሩ ነበር ከየአቅጣጫው ጥሪ የተዥጎደጎደላቸው፡፡ ያን ጊዜ እነመብራት ሃይል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽን ባለስልጣንና ሌሎች በርካታ መስሪያ ቤቶች ጥሪ እንዳደረጉላቸው ሲገልጹልኝ ዛሬ ላይ ቆሜ ቁጭት ይሁን ቅናት የተሰማኝን ስሜት መግለጽ ይከብደኛል፡፡ “…የአንዳቸውንም ጥሪ ከመቀበሌ በፊት ቀጣሪዎቹን ቃለ መጠይቅ አደርግ የነበርኩት እኔው ራሴ ነበርኩ።” አሉኝ ኢንጂኒየር ከብዙ ዓመታት በፊት የነበራቸውን ተመክሮ እያስታወሱ፡፡ “…የዚያን ጊዜው ቴሌኮምኒኬሽን በስዊድኖች ነበር የሚተዳደረው፡፡ ስዊድኖቹ ጥሩ ሊባል የሚችል አቀባበል አደረጉልኝ፡፡ በዚሁ የቴሌኮምዩኒኬሽን ቦርድ ባልደረባ ለመሆን በቃሁ፡፡” ሲሉ እንዴት ቴሌኮምዩኒኬሽን መስሪያ ቤት እንደተቀጠሩና የአማርኛ ቴሌፕሪንተርን ለመፈልሰፍ መነሻ መስሪያ ቤት እንደሆናቸው አበሰሩኝ፡፡
ቴሌፕሪንተርና - ወጣቱ ኢንጅነር ተረፈ ራስወርቅ
አሁን ወጣቱ መሃንዲስ ተረፈ የአማርኛ ቴሌፕሪንተር ለመስራት ተነሳስቶ ምርምሩን ጀምሯል፡፡ በወቅቱ ፕሪንተሮቹ ለላቲን ፊደል ነው የተፈጠሩት የሚል ግትር መከራከሪያ ተነስቶ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው የላቲን ፊደል 26 ነው፡፡ የአማርኛ ደግሞ 270 ነው፡፡ ታዲያ የመከራከሪያ ሃሳቡ ፕሪንተሩ ለ270 ፊደላት ቦታ የለውም የሚል ነበር፡፡
ኢንጂኒየር ይህ ሃሳብ ሲነገረው ጊዜ ሰጥቶ ምርምሩን ቀጠለበት፡፡ እርሱ ያደረግው ዋናው ጥናትም የኢትዮጵያን ፊደሎች እንዴት ቴሌፕሪንተር ውስጥ ማስገባት ይቻላል የሚል ነበር፡፡ ኢንጂኒየር ያኔ ለማስተዋል እንደሞከረው የኢትዮጵያ ፊደሎች ቅርጽና ውበት እጅግ የሚያስደንቅ ነው፡፡ በብዛት 270 ቢሆኑም፣ ቅርጻቸው ግን ከ20 አይበልጥም፡፡ ያኔ እርሱ ለማቅረብ እንደሞከረው የላቲን ፊደሎች 26 ይባሉ እንጂ “ካፒታል ሌተር፤ ስሞል ሌተር” ሲባል ወደ አርባ ይጠጋሉ፡፡ የእኛ ግን ይላሉ የያኔው ወጣት ተመራማሪ “ቅርጹ ሲታይ በጣም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ‘ሀ’ ሲገለበጥ ‘በ’ ይሆናል፡፡ በአናቱ ላይ ዘንግ ሲደረግበት ‘ሰ’ ይሆናል፡፡ ‘ሰ’ ላይ መስመር ሲደረግበት ‘ሸ’ ይሆናል፡፡” በማለት ጥናታዊ ምርምራቸውን ያጠናክራሉ፡፡
እነዚህን ቅርጾች በማስተካከል ብቻ ቴሌፕሪንተሩን መስራት እንደሚቻል ወጣቱ ተመራማሪ የዛሬ ሃምሳ ዓመት አረጋገጠ፡፡ ከዚህ በኋላ ኢንጂነር የዚያን ዘመን ቴሌፕሪንተር የፊደላት ድርድር (ኪቦርድ) ቅርጽ ማስተካከል ያዘ፡፡ ማሽኑ ላይ የሚቀረጹት ፊደሎች ቁመታቸውና አቀማመጣቸው ወረቀቱ ላይ የቱ ጋ እንደሚቀመጡ በደንብ ካተስተካከለ በኋላ ሲጻፍ ፈጽሞ እንደማያስቸግር በሚገባ አረጋገጠ፡፡
ከዚህ በኋላ ኢንጂኒየር የሄዱበትን መንገድ በራሳቸው እንደሚከተለው ያወጉናል፡፡
የኢንጂኒየር ቴሌፕሪንተር
የኪቦርዱን ቅርጽ ካስተካከሉት በኋላ በዛን ጊዜ ፓተንት አልነበረም፤ የአዕምሯዊ ንብረት ህግ ስለነበር የፈጠራ ውጤቴን በይፋ አሰመዘገብኩ፡፡ በኋላም ሶፍትዌሩን ሲመንስ ለሚባለው የጀርመን ኩባንያ አስረከብኩ፡፡ በ1960 ዓ.ም መኪናው (ቴሌፕሪንተሩ) የአማርኛ ፊደል ይዞ ሀገር ቤት ሲመጣ ልዩ ስሜትና የስራ ተበረታችነት ተሰማኝ፡፡
ወዲያው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴሌፕሪንተሩን መረቁ፤ በምረቃው ዕለት አንዱ ቴሌፕሪንተር አሥመራ ቤተመንግስት ተደረገ፡፡ አንደኛው አዲስ አበባ ተቀመጠ፡፡ በወቅቱ የኤርትራው ገዢ ራስ አስራተ ካሳ በአዲሱ መኪና መልዕክት ወደ አዲሰ አበባ ሲልኩ ግርማዊነታቸው መልዕክቱን አይተው የደስታ ስሜታቸውን መደበቅ አልተቻላቸውም ነበር፡፡፡
የሞቀ ትዝታቸውን ሰብሬ በጥያቄ ወደ እኔ ልመልሳቸው ግድ አለኝ፡፡ “ለነገሩ ይህ ቴሌፕሪንተር ምንድነው? እንዴት ነው የሚሰራው? ብያኔው ከምን የመጣነው...” ጥያቄዬን ደረደርኩት። በእርጋታ ሲያዳምጡኝ የተሰማኝን የነጻነት ስሜት የምገልጽበት ቃል ያጥረኛል፡፡እጅግ የሚመቹ አዛውንት ናቸው፡፡
“ቴሌፕሪንተር በርቀት የሚያትምና የሚያሰራጭ መሳሪያነው” ሲሉ ብያኔውን በአጭሩ አስቀመጡልኝ፡፡ ቴሌፕሪንተር በዋናነት አንድን መልእክት በመተየብ ለማሰራጨትና ለመቀበል የሚያገለግል መሳሪያ ነው፡፡ ኢንጂነር ሶፍትዌሩን የፈጠሩ ሲሆኑ፤ ሲመንስ ኩባንያ ደግሞ የቴሌፕሪንተሩን ቅርፅ ያወጣው ኩባንያ ነው፡፡ ይሁንና ፊደሎቹ እንዴት መቀመጥ እንዳለባቸውና የቁመታቸውን መጠን በዝርዝር አጥንተው ያቀረቡት እሳቸው ናቸው፡፡ ለስራ ውጤታቸውም በወቅቱ ጠቀም ያለ የገንዘብ ክፍያ ተደርጎላቸዋል፡፡
የቴሌፕሪንተሩን መግባት በተመለከተ በተከናወነ የምረቃ ሥነሥርዓት ጃንሆይ የሰጡትን አስተያየት ኢንጂነር እንዲህ ያስታውሱታል«… ግርማዊነታቸው በጣም ነው የደነቃቸው የታይፕራይተር ጽሑፍ አይወዱም ነበር ይባላል፤ የሳቸው ንግግር ሁሉ በቁም ጽሑፍ ነበር የሚቀርበው፡፡ የዚህኛው እኔ የሠራሁት ግን የጽሑፍ አጣጣሉ በጣም ደስ አላቸው፡፡ እኔንም ጠጋ ብለው ለዚህ ላበረከትከው አስተዋፅኦ ምን ተደርጎልሀል ሲሉ አናገሩኝ፡፡ ጃንሆይ ለሀገሬ ባቀረብኩት ፈጠራ ደስ ሲላቸው እኔንም ከልብ አረካኝ፡፡ ያን ጊዜ የትራንስሚሽን ክፍል ዋና ሀላፊ ነበርኩ፡፡ ያቺን ቴሌፕሪንተር ለብሔራዊ ሙዚየም የመስጠት ዕቅድ አለኝ፤ እንግዲህ አንድ ቀን ይሄ ተግባር ይከናወናል ብዬ አስባለሁ» አሉኝ፡፡
“የዛሬ 53 ዓመት ኢትዮጵያ የቴሌፕሪንተር ሶፍትዌር የሰራ የሰለጠነ ባለሙያ ነበራት” የሚል ዜና ዛሬ ላይ ቆመን ስንሰማ ውስጣችን የሚጭረው የደስታ ስሜት የላቀ ነው፡፡ ይህ ትውልድ የዚህ ስልጣኔ ብቃት ወራሽ የማይሆንበት ምክንያት ምንድነው? የሚል ጥያቄ ብናነሳ “ለተነሳሳሽነት አርአያ የሚሁኑ የታላላቆቻችን ታሪክና ስራዎቻቸው በወቅቱና በአግባቡ ለትውልድ በመረጃነት ስለማይቆዩ ነው” የሚለው ነጥብ ዋነኛው ምክንያት ነው ብል ‘ተሳስተሃል’ የሚል ካለ እነሆ ብእሩን እንዲያካፍለን እጋብዛለሁ፡፡
ክፍል ሁለት ይቀጥላል።