ኢንጂነር ተረፈና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት - ከስሜነህ ጌታነህ

Life, Health, Religion, Social, General Question
Forum rules
No cursing, bad language and offend other users !
No pornographic images or links!
This forum monitored regularly. We will BAN users without warning for not obeying rules.
እባክዎ የፎረሙን ህጎች ያክብሩ::
Post Reply
selam sew
Leader
Leader
Posts: 616
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

ኢንጂነር ተረፈና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት - ከስሜነህ ጌታነህ

Unread post by selam sew » 09 Dec 2015 17:19

ኢንጂነር ተረፈና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ።
(ስሜነህ ጌታነህ)

« ክፍል አንድ»


Image

አሁን የማወራችሁ ስለ ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ነው። ቴሌ ፕሪንተርን የ ዛሬ 50 አመት ሰርተው በዛን ጊዜ ፓተንት የወሰዱ ናቸው ። በአለም አቀፉ የቴሌኮሚኒኬሽን. ህብረት ውስጥ ለ 40 አመት በትልቅ ሃላፊነ ት ሰርተዋል ። ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጋር አንድ ታሪክ አላቸው። ሰውየው የሀገር ባለውለታና ዛሬም ደከመኝ የማይሉ ናቸውና ታሪካቸውን ብታነቡትስ ።
አንድ ቀን ኢንጂኒየር ስልክ ደውለውልኝ “ለምን አንኮበር ደረስ ብለን አንመለስም?” አሉኝ፡፡ አንኮበር ስለሚገኘው ሎጃቸውና የምኒልክ ቤተመንግስት አጫውተውኝ ነበርና ያንኑ እንድጎበኝ ፈልገዋል፡፡ “ታሪክ የማወቅ ጉጉቴን የተረዱ ታላቅ ሰው” ስል አመስግኜ ወደ አንኮበር ለመሄድ ራሴን አዘጋጀሁ፤ ጓዜን አሰናዳሁ፡፡ በቀጠሮአችን ተገናኝተን ወደ ቦታው ስናመራ በበርካታ ጉዳዮች ላይ እየተጫወትን፤ ሃሳብ እያነሳንና እየጣልን አንኮበር ደረስን፡፡


ማስታወሻ በአንኮበር
የአጼ ምኒልክ ቤተመንግስት በ1936 ዓ.ም በጣሊያኖች ሲቃጠል ኢንጂኒየር የሰባተኛ ዓመት እድሜያቸውን እያከበሩ ነበር፡፡ እናም የልጅነት ቁጭታቸውን ሊወጡ አስበው የአንኮበር ሎጅን ለመመስረት ወገባቸውን ታጥቀው ተነሱ፡፡ ኢንጂኒየር ከሰባት ዓመታት በፊት የአንኮበር ሎጅን ሲመሰርቱ ውስጣቸው በትልቅ እርካታ ተሞላ፡፡
እስከዛሬ አርባ ፎቅ በደረጃ መውጣቴን አላስታውስም፡፡ አንኮበር ቤተመንግስት የተሠራው ከፍታ ቦታ ላይ ስለሆነ ሽቅብ የሚደረገው ጉዞ ቢሰላ በግምት ግን ወደላይ አርባ ፎቅ ይሆናል፡፡ አርባውን ፎቅ እንደጨረስን ነው ቤተመንግስቱን የምናገኘው፡፡ በትንሹ ወደ ፎቁ ለመውጣት 25 ደቂቃ ይወስዳል፡፡ ከቀኑ ስድሰት ሰአት ተኩል ላይ ሎጁ ጋር እንደደረስን መጠነኛ እረፍት ወስጄ የኢንጂኒየርን ያልነጠፈ ወግ በተመስጦ ማድመጥ ቀጠልኩ፡፡ “ስለእኚህ ሰው ምን አስተዋልክ?” ብትሉኝ፤ ስክን ያለ ሰብእናቸውን ነው፡፡ ቶሎ አይደሰቱም፤ በቶሎ አይናደዱም፡፡ ቸኩለው ሃሳብ አይሰነዝሩም፡፡ ቆም ብለው አሰብ ሲያደርጉ በርጋታ ይሞላሉ፡፡
ቴሌ ፕሪንተርን ለሀገራችን ያስተዋወቁ
በወቅቱ የአማርኛ ቴሌፕሪንተሩን ሲሰሩ 32ኛ ዓመታቸውን ያከበሩት ኢንጂኒየር ተረፈ ራስወርቅ ይህን ቴክኖሎጂ በማስተዋወቃቸው ልዩ አድናቆትን አትርፈዋል፡፡ ተወዳጁ ደራሲና ጋዜጠኛ በአሉ ግርማ የዛሬ 46 ዓመት በመነን የእንግሊዝኛ መጽሔት ላይ ቴሌ ፕሪንተር ስለሰሩት ኢንጂነር ፣ አስደናቂ በሆነው ችሎታው “…የራስዋ ፊደል ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በወጣት መሃንዲስ አማካኝነት፣ የአማርኛ ቴሌፕሪንተር ባለቤት ሆነች” ሲል አብስሮ ነበር፡፡ በሙያቸው ለአስር ዓመታት በሀገራቸው ያገለገሉት ኢንጂኒየሩ፣ ቴሌፕሪንተሩን በሰሩ ማግስት የዓለም አቀፉ የቴሌኮምኒኬሽን ህብረት ባልደረባ ለመሆን በቁ፡፡ በህብረቱ መቀመጫ ስዊዘርላንድ አገር ለአርባ ዓመታት ከማገልገላቸውም በላይ የጎለበተ ልምድ አካብተዋል፤ ልምዳቸውንም አካፍለዋል፤ ልጆቻቸውንም ወልደው አሳድገዋል:: ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ዓለም አቀፉን የቴሌኮምኒኬሽንን ህብረት በሃላፊነት በማገልገል ኢንጂኒየር የመጀመሪያው ናቸው፡፡ ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡
ኢንጂኒየር ሲታዩ የ79 ዓመት አዛውንት አይመስሉም፡፡ “ጠንካራ ነዎት!” ስላቸው ዘወትር የአካል ማጎልበቻ እንቅስቃሴ ማድረጋቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንደረዳቸው ነገሩኝ፡፡ በተለይ የሌሊቱ ሰዓት ለስፖርት ምቹ ጊዜ እንደሆነላቸው ጠቆም አደረጉኝ፡፡ ቀኑንማ ዛሬም በጡረታ እድሜያቸው በሥራ ነው የሚያሳልፉት፡፡
ትውልዳቸው ሰሜን ሸዋ፤ አንኮበር ነው፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት ቤት እንደደረሰ በትውልድ ቀዬአቸው ፊደል ከቆጠሩ በኋላ የአስር አመት እድሜ ሲሞላቸው (የዛሬ 69 ዓመት መሆኑ ነው) ወደ አዲስ አበባ መጥተው በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡ ያኔ የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ቤት ታሪክ፤ ተፈሪ መኮንን የሰማንያ ስምንት ዓመት እድሜ ጠገብ አንጋፋ የትምህርት ተቋም ነው፡፡ ኢንጂኒየርም በትምህርት ቤቱ እንደ ማለፋቸው ብዙ ትዝታ አላቸው፡፡
ታዳጊው ተረፈ በልጅነታቸው እርሻ ለመማር ነበር ያሰቡት፡፡ ግና አንድ ሚስተር ዳሮ የሚባል አስተማሪያቸው የእርሻ ትምህርት እንደማይሆናቸው ሲመክራቸው የሳይንሰ ትምህርትን ምርጫቸው አደረጉ፡፡ አዛውንቱ ኢንጂኒየር “እስከ ዛሬ ይህን ሰው አመሰግነዋለሁ” ይላሉ፡፡ ኢንጂነር ከተፈሪ መኮንን አስራ ሁለተኛ ክፍልን እንደጨረሱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን ተቀላቀሉ፡፡ በዚያን ዘመን በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት የትምህርት መምረጫ ጊዜ ነበርና የሳይንስ ትምህርት ምርጫቸውን የኤሌክትሪክ መሃንዲስ ትምህርትን ተያያዙት፡፡
አገር ቤት ለሁለት ዓመታት ከተማሩ በኋላ፣ ወደ አሜሪካ አገር በመሄድ በኤሌክትሪክ ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለማግኘት በቅተዋል፡፡ ኢንጂኒየር አሜሪካ የተማሩት ትምህርት ቤት፤ በ1824 በተቋቋመውና ሮይ ኒዮርክ ክፍለ ግዛት ውስጥ በሚገኘው በመጀመሪያው የአሜሪካ የቴክኒክ ትምህርት ቤት - ሬንስለር ፖሊቴክኒክ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ የግል ቢሆንም ኢንጂኒየር ባገኙት የነጻ ትምህርት እድል በማግኘት ነበር ወደዚያው ያቀኑት፡፡ የሁለተኛ ዓመት የአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪ ተረፈ ራስወርቅ፤ ሬንስለር ፖሊቴክኒክ ሲደርሱ ከሶስተኛ አመት ተማሪዎች ጋር ነበር ትምህርታቸውን የቀጠሉት፡፡ በኢንጂኒየር ተረፈ እምነት ትልቁ የመሃንዲስነት ትምህርት አእምሮን ማሰራት ነው፡፡ አንጎልን ማስፋት ነው፡፡“አንጎልን ካሰለጠነው ብዙ ማሰብ እንደሚችል ተምረናል” ይላሉ ኢንጂነር፡፡ የተማሩበት ትምህርት ቤት ዓላማ ተማሪዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ ነው፡፡ እርሳቸውም ትምህርት ቤቱ በእጅጉ እንደጠቀማቸውና ያምናሉ፡፡ ውስጣቸው ያለውን አቅምም አውጥተው እንደተጠቀሙበት ያምናሉ፡፡
ኢንጂኒየር ተረፈም ሀገሬን በሙያዬ ላገለግል እችላለሁ ብለው ስለሚያምኑ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ አገር ቤት የመመለስ ውጥን ነበራቸው፡፡ በ1953 ዓ.ም ትምህርታቸውን አጠናቀው ከባህር ማዶ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የተደረገላቸውን አቀባበል በልዩ የደስታ ስሜት ነው የሚገልጹት፡፡ አቀባበሉ በልዩ ማእረግ ነበር፤ እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ነበር በልዩ ክብር እንዲያርፉ የተደረገው፡፡
በወቅቱ ሥራ አማርጠው እንዲጀምሩ ነበር ከየአቅጣጫው ጥሪ የተዥጎደጎደላቸው፡፡ ያን ጊዜ እነመብራት ሃይል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮምኒኬሽን ባለስልጣንና ሌሎች በርካታ መስሪያ ቤቶች ጥሪ እንዳደረጉላቸው ሲገልጹልኝ ዛሬ ላይ ቆሜ ቁጭት ይሁን ቅናት የተሰማኝን ስሜት መግለጽ ይከብደኛል፡፡ “…የአንዳቸውንም ጥሪ ከመቀበሌ በፊት ቀጣሪዎቹን ቃለ መጠይቅ አደርግ የነበርኩት እኔው ራሴ ነበርኩ።” አሉኝ ኢንጂኒየር ከብዙ ዓመታት በፊት የነበራቸውን ተመክሮ እያስታወሱ፡፡ “…የዚያን ጊዜው ቴሌኮምኒኬሽን በስዊድኖች ነበር የሚተዳደረው፡፡ ስዊድኖቹ ጥሩ ሊባል የሚችል አቀባበል አደረጉልኝ፡፡ በዚሁ የቴሌኮምዩኒኬሽን ቦርድ ባልደረባ ለመሆን በቃሁ፡፡” ሲሉ እንዴት ቴሌኮምዩኒኬሽን መስሪያ ቤት እንደተቀጠሩና የአማርኛ ቴሌፕሪንተርን ለመፈልሰፍ መነሻ መስሪያ ቤት እንደሆናቸው አበሰሩኝ፡፡
ቴሌፕሪንተርና - ወጣቱ ኢንጅነር ተረፈ ራስወርቅ
አሁን ወጣቱ መሃንዲስ ተረፈ የአማርኛ ቴሌፕሪንተር ለመስራት ተነሳስቶ ምርምሩን ጀምሯል፡፡ በወቅቱ ፕሪንተሮቹ ለላቲን ፊደል ነው የተፈጠሩት የሚል ግትር መከራከሪያ ተነስቶ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው የላቲን ፊደል 26 ነው፡፡ የአማርኛ ደግሞ 270 ነው፡፡ ታዲያ የመከራከሪያ ሃሳቡ ፕሪንተሩ ለ270 ፊደላት ቦታ የለውም የሚል ነበር፡፡
ኢንጂኒየር ይህ ሃሳብ ሲነገረው ጊዜ ሰጥቶ ምርምሩን ቀጠለበት፡፡ እርሱ ያደረግው ዋናው ጥናትም የኢትዮጵያን ፊደሎች እንዴት ቴሌፕሪንተር ውስጥ ማስገባት ይቻላል የሚል ነበር፡፡ ኢንጂኒየር ያኔ ለማስተዋል እንደሞከረው የኢትዮጵያ ፊደሎች ቅርጽና ውበት እጅግ የሚያስደንቅ ነው፡፡ በብዛት 270 ቢሆኑም፣ ቅርጻቸው ግን ከ20 አይበልጥም፡፡ ያኔ እርሱ ለማቅረብ እንደሞከረው የላቲን ፊደሎች 26 ይባሉ እንጂ “ካፒታል ሌተር፤ ስሞል ሌተር” ሲባል ወደ አርባ ይጠጋሉ፡፡ የእኛ ግን ይላሉ የያኔው ወጣት ተመራማሪ “ቅርጹ ሲታይ በጣም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ‘ሀ’ ሲገለበጥ ‘በ’ ይሆናል፡፡ በአናቱ ላይ ዘንግ ሲደረግበት ‘ሰ’ ይሆናል፡፡ ‘ሰ’ ላይ መስመር ሲደረግበት ‘ሸ’ ይሆናል፡፡” በማለት ጥናታዊ ምርምራቸውን ያጠናክራሉ፡፡
እነዚህን ቅርጾች በማስተካከል ብቻ ቴሌፕሪንተሩን መስራት እንደሚቻል ወጣቱ ተመራማሪ የዛሬ ሃምሳ ዓመት አረጋገጠ፡፡ ከዚህ በኋላ ኢንጂነር የዚያን ዘመን ቴሌፕሪንተር የፊደላት ድርድር (ኪቦርድ) ቅርጽ ማስተካከል ያዘ፡፡ ማሽኑ ላይ የሚቀረጹት ፊደሎች ቁመታቸውና አቀማመጣቸው ወረቀቱ ላይ የቱ ጋ እንደሚቀመጡ በደንብ ካተስተካከለ በኋላ ሲጻፍ ፈጽሞ እንደማያስቸግር በሚገባ አረጋገጠ፡፡
ከዚህ በኋላ ኢንጂኒየር የሄዱበትን መንገድ በራሳቸው እንደሚከተለው ያወጉናል፡፡
የኢንጂኒየር ቴሌፕሪንተር
የኪቦርዱን ቅርጽ ካስተካከሉት በኋላ በዛን ጊዜ ፓተንት አልነበረም፤ የአዕምሯዊ ንብረት ህግ ስለነበር የፈጠራ ውጤቴን በይፋ አሰመዘገብኩ፡፡ በኋላም ሶፍትዌሩን ሲመንስ ለሚባለው የጀርመን ኩባንያ አስረከብኩ፡፡ በ1960 ዓ.ም መኪናው (ቴሌፕሪንተሩ) የአማርኛ ፊደል ይዞ ሀገር ቤት ሲመጣ ልዩ ስሜትና የስራ ተበረታችነት ተሰማኝ፡፡
ወዲያው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴሌፕሪንተሩን መረቁ፤ በምረቃው ዕለት አንዱ ቴሌፕሪንተር አሥመራ ቤተመንግስት ተደረገ፡፡ አንደኛው አዲስ አበባ ተቀመጠ፡፡ በወቅቱ የኤርትራው ገዢ ራስ አስራተ ካሳ በአዲሱ መኪና መልዕክት ወደ አዲሰ አበባ ሲልኩ ግርማዊነታቸው መልዕክቱን አይተው የደስታ ስሜታቸውን መደበቅ አልተቻላቸውም ነበር፡፡፡
የሞቀ ትዝታቸውን ሰብሬ በጥያቄ ወደ እኔ ልመልሳቸው ግድ አለኝ፡፡ “ለነገሩ ይህ ቴሌፕሪንተር ምንድነው? እንዴት ነው የሚሰራው? ብያኔው ከምን የመጣነው...” ጥያቄዬን ደረደርኩት። በእርጋታ ሲያዳምጡኝ የተሰማኝን የነጻነት ስሜት የምገልጽበት ቃል ያጥረኛል፡፡እጅግ የሚመቹ አዛውንት ናቸው፡፡
“ቴሌፕሪንተር በርቀት የሚያትምና የሚያሰራጭ መሳሪያነው” ሲሉ ብያኔውን በአጭሩ አስቀመጡልኝ፡፡ ቴሌፕሪንተር በዋናነት አንድን መልእክት በመተየብ ለማሰራጨትና ለመቀበል የሚያገለግል መሳሪያ ነው፡፡ ኢንጂነር ሶፍትዌሩን የፈጠሩ ሲሆኑ፤ ሲመንስ ኩባንያ ደግሞ የቴሌፕሪንተሩን ቅርፅ ያወጣው ኩባንያ ነው፡፡ ይሁንና ፊደሎቹ እንዴት መቀመጥ እንዳለባቸውና የቁመታቸውን መጠን በዝርዝር አጥንተው ያቀረቡት እሳቸው ናቸው፡፡ ለስራ ውጤታቸውም በወቅቱ ጠቀም ያለ የገንዘብ ክፍያ ተደርጎላቸዋል፡፡
የቴሌፕሪንተሩን መግባት በተመለከተ በተከናወነ የምረቃ ሥነሥርዓት ጃንሆይ የሰጡትን አስተያየት ኢንጂነር እንዲህ ያስታውሱታል«… ግርማዊነታቸው በጣም ነው የደነቃቸው የታይፕራይተር ጽሑፍ አይወዱም ነበር ይባላል፤ የሳቸው ንግግር ሁሉ በቁም ጽሑፍ ነበር የሚቀርበው፡፡ የዚህኛው እኔ የሠራሁት ግን የጽሑፍ አጣጣሉ በጣም ደስ አላቸው፡፡ እኔንም ጠጋ ብለው ለዚህ ላበረከትከው አስተዋፅኦ ምን ተደርጎልሀል ሲሉ አናገሩኝ፡፡ ጃንሆይ ለሀገሬ ባቀረብኩት ፈጠራ ደስ ሲላቸው እኔንም ከልብ አረካኝ፡፡ ያን ጊዜ የትራንስሚሽን ክፍል ዋና ሀላፊ ነበርኩ፡፡ ያቺን ቴሌፕሪንተር ለብሔራዊ ሙዚየም የመስጠት ዕቅድ አለኝ፤ እንግዲህ አንድ ቀን ይሄ ተግባር ይከናወናል ብዬ አስባለሁ» አሉኝ፡፡
“የዛሬ 53 ዓመት ኢትዮጵያ የቴሌፕሪንተር ሶፍትዌር የሰራ የሰለጠነ ባለሙያ ነበራት” የሚል ዜና ዛሬ ላይ ቆመን ስንሰማ ውስጣችን የሚጭረው የደስታ ስሜት የላቀ ነው፡፡ ይህ ትውልድ የዚህ ስልጣኔ ብቃት ወራሽ የማይሆንበት ምክንያት ምንድነው? የሚል ጥያቄ ብናነሳ “ለተነሳሳሽነት አርአያ የሚሁኑ የታላላቆቻችን ታሪክና ስራዎቻቸው በወቅቱና በአግባቡ ለትውልድ በመረጃነት ስለማይቆዩ ነው” የሚለው ነጥብ ዋነኛው ምክንያት ነው ብል ‘ተሳስተሃል’ የሚል ካለ እነሆ ብእሩን እንዲያካፍለን እጋብዛለሁ፡፡

ክፍል ሁለት ይቀጥላል።

selam sew
Leader
Leader
Posts: 616
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

Re: ኢንጂነር ተረፈና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት - ከስሜነህ ጌታነህ

Unread post by selam sew » 09 Dec 2015 17:21

Image

« ክፍል ሁለት»
አሁን የማወራችሁ ስለ ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ነው። ቴሌ ፕሪንተርን የ ዛሬ 50 አመት ሰርተው በዛን ጊዜ ፓተንት የወሰዱ ናቸው ። በአለም አቀፉ የቴሌኮሚኒኬሽን. ህብረት ውስጥ ለ 40 አመት በትልቅ ሃላፊነ ት ሰርተዋል ። ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጋር አንድ ታሪክ አላቸው። ሰውየው የሀገር ባለውለታና ዛሬም ደከመኝ የማይሉ ናቸውና ታሪካቸውን ብታነቡትስ ።

ኢንጂኒየር ተረፈ በቴሌኮምኒኬሽን ቦርድ ከ1953 – 1955 እየሰሩ ሳሉ በ1955 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመሰረተ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለማቋቋም በሚታሰብበት ጊዜ የቴሌ ቢሮ የሬድዮ ስርጭት ክፍል በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዳራሽ ውስጥ ተደራጅቶ ነበር፡፡ ምክንያቱም ጉባዔውን ለመዘገብ በርካታ ጋዜጠኞች ወደ አዲሰ አበባ ይመጡ ስለነበር፡፡

ለዚህ ታሪካዊ ጉባዔ የትርጉም መስመሩ ኃላፊ የነበሩት ኢንጂኒየር ተረፈ ነበሩ፡፡ ለዚህ ታላቅ የድርጅት ምስረታ ጉባኤ ከሰላሳ በላይ የአፍሪካ መሪዎች ሲመጡ ወደ ሀገራቸው በመደወል ከባለስልጣኖቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ የቴሌና የፋክስ ግንኙነት አገልግሎት ይፈለጋል፡፡ ኢንጂነር ደግሞ ያኔ የትራንስሚሽን ክፍል ኃላፊ ነበሩ፡፡

ኢንጂኒየር ወደኋላ መለስ ብለው የአፍሪካ አንድነት ምስረታን ሲያወጉኝ ብዙ ሃሳቦች መጡላቸው “በእንዲህ ዓይነት ኮንፈረንስ ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የሚናገረው በቴፕ ይቀዳል፡፡ ሊቀመንበሩ ‘ዕድሉን ለእከሌ ስጡ’ ሲሉ የሚጫን ሰው አለ፡፡ ዕቃውን በሙሉ በስብሰባው ውስጥ መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ በዛን ጊዜ አስቀድመው የመጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ነበሩ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ስብሰባ በሊቀመንበርነት የመሩት ደግሞ የቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ከተማ ይፍሩ ነበሩ” ሲሉ ኢንጂነር ትዝታቸውን አወጉኝ፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና የኢንጂኒየር የበኩር ልጅ
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (ያሁኑ የአፍሪካ ህብረት) የዛሬ 5፫ ዓመት ግድም ግንቦት 18 ቀን 1955 ዓ.ም ሲመሰረት ለእንግዳ መሪዎች የቴሌኮምዩኒኬሽንና ፋክስ አገለግሎት እንዲመቻች አስተዋጽኦ ያደረጉት ኢንጂኒየር ተረፈ ያንን ዘመን ሲያስቡ የገጠማቸውን የደስታና የሃላፊነት ስሜት በትዝታ አወጉኝ፡፡ በወቅቱ የአፍሪካ መሪዎችን የቃል ኪዳን ሰነድ በሚፈረምበት ለሊት ኢንጂነር በስራ ተጠምደው እዚያው ውለው እዚያው አድረው ነበር፡፡

እቤታቸው ደግሞ ሌላ የህይወት ገጽታ ነበረው፡፡ ነፍሰ ጡሯ ባለቤታቸው ወ/ሮ ብርሃኔ በምጥ ተይዘዋል፡፡ በኋላም የቅርብ ዘመዶች ወደ ሆሰፒታል ይዘዋቸው ይሄዳሉ፡፡ ኢንጂኒየር ቻርተሩ ከተፈረመ በኋላ ሌሊቱን ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ትልቅ የምስራች ጠበቃቸው፡፡ ወ/ሮ ብርሃኔ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ከተገላገሉ በኋላ ወንድ ልጅ ታቅፈው ጠበቋቸው፡፡ የበኩር ልጃቸውን ልጁም አንድነት ተረፈ ራስወርቅ ብለው ሰየሙት፡፡

ያኔ የተወለደው አንድነት ተረፈ ራስወርቅ ዛሬ መሀንዲስ ነው፡፡ ወራሽነቱ በልጅነት ብቻ ሳይሆን በሙያም ሆነ፡፡ ጎልማሳና የሶስት ልጆች አባት ሆኗል፡፡ አንድነት በመጀመሪያ እንደ አባቱ በቴሌ ዘርፍ ውስጥ ነበር የተሰማራው፡፡ አንድ ወቅት ደግሞ በወርልድ ስፔስ ውስጥ በዋና የኦፕሬሽን ኦፊሰርነት አገልግሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት አንድ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ የብረታ ብረቶች ጥራት ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ ኩባንያ ባለቤት ነው፡፡

ሁለተኛው ልጅ ኢዛና ተረፈ ይባላል፡፡ ነዋሪነቱ በካናዳ ሲሆን እሱም በቴሌኮም ዘርፍ ውስጥ ሰርቷል፡፡ የካናዳ የሎው ፔጅስ ምክትል ፕሬዝዳንትም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የራሱን የቴሌኮም ኩባንያ አቋቁሞ ኬንያ፣ ዑጋንዳና ታንዛንያ ላይ እየሰራ ነው፡፡ ሶሰተኛዋ የኢንጂኒየር ልጅ መላዬ ተረፈም ነች፡፡ እሷም እንደ ወንድሞቿ መሀንዲስ ነች፡፡ የሁለት ልጆች እናት ስትሆን፤ የዕቃ ግዢ ጉዳይ ላይ ምክር የሚሰጥ ኩባንያ አላት፡፡ ኢንጂኒየር ተረፈ ልጃቸው አንድነት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የመስራት ፅኑ ፍላጎት እንዳለው አውግተውኛል፡፡

Image

ኢንጂኒየር በጄኔቭ
እንደሚታወቀው የዓለም አቀፍ የቴሌኮምኒኬሽን አንድነት በ1865 ዓ.ም የተፈጠረ መቀመጫውን ጄኔቭ ያደረገ ትልቅ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት ኢንጂኒየር በሄዱበት ዘመን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አንድ ክፍል ነበር፡፡ እናም ያኔ የህብረቱ ዋና ጸሐፊ የቱኒዚያው ሚስተር መሐመድ ሚሊ ይባሉ ነበሩ፡፡ ህብረቱ ሰዎችን ሊቀጥር ሲያወዳድር አንድ የአፍሪካ ክፍል ቦታ ክፍት ሲሆንባቸው ለአባል ሀገሮች ሁሉ ክፍት ቦታ መኖሩን አሳወቁ፤ ኢንጂኒየርም ያኔ ነበር ከተወዳዳሪዎቹ አንዱ ለመሆን የበቁት፡፡ የትምህርት ሁኔታውና የሰሩት ሁሉ በሚገባ ታይቶ የህብረቱ ባልደረባ ሊሆኑ ቻሉ፡፡ ከዛም ኢንጂነር በዓለም አቀፍ የቴሌኮምኒኬሽን ህብረት የአፍሪካ ጉዳይ ክፍል ውስጥ ማገልገል ያዙ፡፡ በጄኔቭ አንድ ብለው የጀመሩት የስራ ዘመን ለ40 ዓመታት ዘልቋል፡፡

እሳቸው እንደሚያስረዱት የክፍሉ ሥራ አፍሪካ በቴሌኮም ዘርፍ ዕድገት እንድታመጣ ማስቻል ነው፡፡ ኢንጂነር ለአርባ ዓመታት በህብረቱ ውስጥ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው በሰሩባቸው ዓመታት የአፍሪካን የቴሌኮም ዕድገት ዕውን ለማድረግ የአቅማቸውን ያህል ሞክረዋል፡፡ የመጀመሪያው የህብረቱ ቀዳሚ ተግባር የቴሌኮምኒኬሽን ማሰልጠኛዎች በየሀገሩ መመስረት ነው፡፡

ሌላው በኢንጂኒየር አመራር ጊዜ የተለወጠው የተለመደው የቅኝ ግዛት የስልክ መስመር መሰበሩ ነው፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ነፃም ከወጡ ወዲያ የቴሌፎን የመገናኛ መስመራቸው ከድሮ ቅኝ ገዢያቸው ጋር ስለነበረ በዛ ላይ መስመሩን የሚያስተላልፉት በብራስልስ፣ በፓሪስ፣ በለንደንና በሮም በኩል ስለነበር ቅኝ ገዢዎቹ መረጃውንም ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ለምሳሌ ፓትሪስ ሉሙምባ የተገደለው የስልክ መስመር ተጠልፎ ነው፡፡ የኢንጂኒየር ትልቁ ስኬት የነበረውን የቅኝ ግዛት መስመር መስበር መቻላቸው ነው፡፡

ኢንጂነር በዚህ መስሪያ ቤት በነበራቸው ቆይታ የበርካታ ሀገራትን የቴሌኮም የዕድገት ደረጃ ለመለየት ችለዋል፡፡ እንደ እሳቸው አባባል በዚያን ዘመን (በ1981 ዓ.ም ግድም ማለታቸው ነው) የቻይና ቴሌኮምኒኬሽን ከኢትዮጵያም ያነሰ እንደነበር ይመሰክራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በቴሌው ዘርፍ ብዙ መሠራቱን ያምኑበታል፡፡ ሆኖም ግን የኔትወርክ መቆራረጥ ችግር የብዙ ሰው መነጋገሪያ መሆኑን አግባብነት ይረዳሉ፤ በሌላ በኩል የአገልግሎት ለውጥና፤ የተጠቃሚ መበራከት በአንድ ላይ ሲከሰት እንዲህ አይነት የኔትዎርክ መጨናነቅ ሊኖር እንደሚችል እምነታቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና ጉዳዮ የሚመለከተው ክፍል ትኩረት ሰጥቶ፤ ተግቶ ሰጥቶ ጊዜው የሚጠይቀውን አገልግሎት በተቀላጠፈ መልኩ መስጠት ይጠብቅበታል ይላሉ፡፡

ኢንጂኒየር ከቤተሰብ ጋር ዘና ማለት ትልቅ ርካታ ይሰጣቸዋል፡፡ በየዓመቱ ከልጅ ልጆቻቸው ጋር ሆነው የተለያዩ አገሮችን ይጎበኛሉ፡፡ “ባለቤቴና ልጆቼ የስኬቴ ምንጭ ናቸው” የሚሉት ኢንጂኒየር ዛሬ ሙሉ በሙሉ መኖሪያቸውን በአዲስ አበባ አድርገዋል፡፡ አንኮበር ሎጅን ለማሳደግ ቀን ተሌት ይደክማሉ፡፡ ማማረርና አልችልም የሚል ቃል የማይወጣቸው ታላቅ ኢትዮጵያዊ ህይወት ጣፋጭ ስለሆነችላቸው ደስ ብሏቸዋል፤ መከራ ቢመጣ ግን ከመጋፈጥ ወደ ኋላ የማይሉ መሆናቸውን እኔ በሚገባ ተገንዝቤያለሁ፡፡

ከኢንጂኒየር ተረፈ ምን እንማራለን? ገድላቸውን ታሪካቸዉን ያካፈልኳችሁ እኚህ ሰው ለአንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ የሚያወርሱት እሴት እንዳለ አውቄአለሁ፡፡ የሄዱበትን መንገድ ልብ ብዬ ሳስተውል፤ የነገሩኝን ሳሰላስል፤ የእሳቸው ህይወት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡ የኢንጂኒየር ተረፈ እሴቶች እንዲህ በመጽሔት ተጽፈው የሚያልቁ አይመስለኝም፡፡ ቀርቦ ላነበባቸው መሃንዲሱ የተረጋጉ መጽሐፍ ናቸው፡፡ እኔ ይህን ጽሑፍ ሳቀርብ አንባቢያን ስለ ኢንጂኒየር እንዲያውቁት ወይም ሊወስዱት ይገባል ያልኩትን ነጥብ በስድስት ከፍዬ እንዳስቀምጥ ይፈቀድልኝ፡፡

እሴት 1፤ ኢንጂኒየር ሃገራቸውን ይወዳሉ ብቻ ሳይሆን ፍቅራቸውንም ዋጋ በመክፈል ያሳያሉ፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ያኮራቸዋል ብቻ ሳይሆን እኔስ ምን ባደርግ ይሻላል? ብለው ያሰቡትን ከማድረግ ወደኋላ የማይሉ ናቸው፡፡ አንኮበር ሎጅን ሲመሰርቱ ይህን ጥልቅ የሀገር ፍቅር ይዘው ነው፡፡

እሴት 2፤ ኢንጂኒየር ለሃይማኖታቸው ቀናኢ ናቸው፤ ከወላጅ አባታቸው የተቀበሉትን አደራ ጠበቀው ያቆዩ መሆናቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ ይህንኑ ትልቅ አደራ ሲወጡም በፍቅር እንጂ የመድከም ስሜት ፈጽሞ አይታይባቸውም፡፡

እሴት 3፤ እኚህ እንግዳዬ ብዙ የህይወት ፈርጅን በጥልቀት ያዩ በመሆናቸው ዛሬ ትልቅ መረጋጋት ሰፍኖባቸው አይቻለሁ፡፡ አንድ ወጣት ይህን የተረጋጋና የሰከነ ሰብእና አይቶ ለእድገት ራሱን ይቀሰቅሳል፡፡

እሴት 4፤ ኢንጂኒየር የእችለዋለሁ ስሜታቸዉ በጣም ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሳ ዛሬ በ78 ዓመታቸዉ ትኩስ የመስራት ፍላጎታቸዉ እንዳለ ነዉ፡፡ አይሆንልኝም፤ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ ባክህ፤የሚሳካ አይመስለኝም የሚል ንገግር ከመሀንዲሱ አፍ ወጥቶ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ የማይቻል የሚመስልን ነገር ችሎ ማግኘት የእርሳቸዉ ዋና መርህ ነው፡፡

brad000123
Posts: 2
Joined: 04 Nov 2012 23:40
Contact:

Re: ኢንጂነር ተረፈና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት - ከስሜነህ ጌታነህ

Unread post by brad000123 » 25 Oct 2016 10:01

hiiiiiiii
adviceortips.blogspot.com

Post Reply

Return to “Ethio General .... ኢትዮ ማህበረሰባዊ ርዕሶች”