የጃንሆይ የመጨረሻ ሰዓት

Life, Health, Religion, Social, General Question
Forum rules
No cursing, bad language and offend other users !
No pornographic images or links!
This forum monitored regularly. We will BAN users without warning for not obeying rules.
እባክዎ የፎረሙን ህጎች ያክብሩ::
User avatar
nebex
Leader
Leader
Posts: 283
Joined: 29 Oct 2009 10:32
Contact:

የጃንሆይ የመጨረሻ ሰዓት

Unread post by nebex » 10 Apr 2016 00:54

የጃንሆይ የመጨረሻ ሰዓት

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የግል አሽከርና አልባሽ ስዩም ጣሰው በ14 ዓመት የቤተመንግስት አገልግሎታቸው፣ በዕለት ማስታወሻቸው ላይ ሲያሰፍሩ የቆዩትን መረጃ ጋዜጠኛ ግርማ ለማ አስተካክሎ በ2006 ዓ.ም “የንጉሡ ገመና” በሚል ለንባብ አብቅቶታል፡፡ የጃንሆይ የመጨረሻ ሰዓት ምን እንደሚመስል ለማስታወስ ከዚሁ መጽሐፍ ላይ ተከታዩን ቀንጭበን አቅርበናል፡፡ ጃንሆይ ከስልጣን የወረዱት መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ነው - የዛሬ 40 ዓመት፡፡
…እርሳቸውም የተቀበሉት ከልብ ነው፡፡ ማታ የሻምበል ደምሴ የክብር ዘበኛ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ከጀ/ፍሬሰንበት ቢሮ ድረስ መጥቶ አቶ ክበበው ኃይሌንና አቶ ወንደሰን አንዳርጌን አነጋግሮአል፡፡ ይኸውም ግርማዊነታቸው ምናልባት ሕይወታቸውን በገዛ እጃቸው እንዳያጠፉ በአጠገባቸው የሚገኘውን መሣሪያና መድኃኒቶች በሙሉ እንዲያሸሹ ነግሮአቸው ሄደ፡፡ እነርሱም መድኃኒት ይኑር አይኑር ስለማያውቁ፣ መሳሪያው ብቻ ከአጠገባቸው ወደሌላ ኰሜዲኖ ውስጥ ተዛውሮ እንዲቀመጥ አደረጉ፡፡ እኔም ወደ ቤቴ ሄድኩ፡፡
በ2/1/67 ዓ.ም ጠዋት አድሚራል እስክንድር መጥተው፤ “አዋጅ ስለአለ ሬዲዮ ይከፈትላቸው” ስላሉ ገብተው፣ ሬዲዮ በ1፡30 ሰዓት ሲከፈት ሳይሠራ ትንሽ ቆየት ብሎ ግርማዊነታቸው ከሥልጣን መውረዳቸውን ሲያውጅ፣ ጃንሆይም “ወይ አንተ እግዚአብሔር” ብለው በጥሞና እስከመጨረሻው ድረስ አደመጡ፡፡ ከዚያም ትንሽ ቆይተን ከመኝታ ቤት ወደ ውጭ ወጣን፡፡
ከትንሽ ደቂቃዎች በኋላ አድሚራል እስክንድር መጥተው ጠሩንና ገባን፡፡ ከዚያም ልብስ መልበስ ጀመሩ፡፡ በሚለብሱበት ጊዜ ከመጥቆራቸው በስተቀር ከሰሞኑ ምንም ለውጥ አላሳዩም፡፡ ለብሰው ከጨረሱ በኋላ ፀሎት ለማድረስ ስለቆሙ ትተናቸው ወጣን፡፡ ፀሎት እንደጨረሱ 2፡10 ሰዓት ሲሆን በረንዳ ወጥተው ከተንሸራሸሩ በኋላ፣ ወደ ውስጥ ተመልሰው ከአሽከሮች መኝታ ቤት ሲደርሱ ልዕልት ሰብለ ደስታና ወ/ሮ ሜሪ አበበ ከአድሚራል እስክንድር ጋር ሲመጡ አገኙዋቸው፡፡ እጅ ነስተው ሳሙዋቸው፡፡ ከዚያም ተያይዘው ወደ መኝታ ቤት ገቡ፡፡ ከዚያም አድሚራል መጡና “ቁርስ ገበታ ቤት ከሚሆን መኝታ ቤት ቢሆን ይሻላል” ስላሉ ለቦዮቹ ነገርንና ወደዚያው ተዘጋጅቶ፣ ቁርስ በተለመደው ሰዓት 2፡20 ሰዓት ቀረበ፡፡
እርሳቸውም ከተዘጋጀላቸው ከመልበሻ ቤት ገቡና ተቀመጡ፡፡ ሲያዩዋቸው ታዲያ የመዝናናት መልክ ነበራቸው፡፡ ቁርሳቸውንም ከወትሮው ባልተለየ ሁኔታ በሉ፡፡ እንደውም ከውሻቸው ጋር እየቀለዱ ሥጋ ሲያጐርሱ፣ ሲስቁ በጣም ገረመኝ፡፡ እንኳን ከሥልጣን የወረዱ ምንም የሆኑ አልመሰላቸውም ነበረ፡፡ ቁርስ በልተው እንደጨረሱ ፀሎት አደረሱና በ 2፡38 ወደ ሳሎን ወጡ፡፡
በ2፡43 ሰዓት ደግሞ ከመኝታ ቤት ተመለሱና እቢሮአቸው ቁጭ ብለው “ቦርሳዬን አምጣልኝ” አሉኝና ወስጄ ሰጥቼ ሲከፍቱት ወጣሁ፡፡ ትንሽ እንደቆየሁ አንድ ነገር ተሰማኝ፡፡ ይኸውም ምናልባት መድኃኒት ከቦርሳቸው ውስጥ አስቀምጠው እንደሆነ አውጥተው የጠጡ እንደሆነ ብዬ ስለተጠራጠርኩ፣ አድሚራልን ጠርቼ ገብተው ከእርሳቸው ጋር እንዲቆዩ ስለነገርኳቸው፣ ከእህቶቻቸው ጋር ተያይዘው ገቡ፡፡
እነርሱም ሲገቡ ቦርሳቸውን ከፍተው ከውስጡ ዕቃ ይፈልጉ ነበር፡፡ መሳሪያቸውን ግን ማታ ካደረበት ቦታ አንስተው ከዱሮው ቦታ አሽከሮቹ መልሰው አስቀምጠውት ስለነበር፣ ለፀሎት እንደቆሙ ተመካክረን፣ እኔ ሁለት ሽጉጥና አንድ በቦርሳ ውስጥ ያለ አውቶማቲክ ሽጉጥ (በጣም ትልቅ ነው) አወጣሁና፣ ከተረኛው አሽከር መኝታ ቤት ካለው የወረቀት መመርመሪያ ውስጥ አስቀመጥኩት፡፡ ስለዚህ ከመድኃኒት ሌላ መሳሪያ ስለሌለ የሰጋሁት መድኃኒት ይጠጣሉ ብዬ ነበር፡፡
ጃንሆይና ልዑል ራስ እምሩ ቢሮ ገብተው ትንሽ ቆይተው፣ በ4፡00 ሰዓት የደርጉ አባሎች በጀ/ኃይለጊዮርጊስ ተጠርተው ከቢሮ ገቡ፡፡ ወደዚያው ሠላምታ ሰጡና አንድ የፖሊስ ሠራዊት ባልደረባ ሻለቃ አዋጁን አነበበላቸው፡፡ ይኸው ሻለቃ በቀደም ስለውጭ አገር ገንዘብ መመለስ ጉዳይ ለመነጋገር የመጡት የደርጉ አባሎች መሪና ወረቀቱንም ያነበበው ደበላ ዲንሳ ነበር፡፡ አዋጁን ለማንበብና ጃንሆይን ይዘው ለመሄድ በገቡ ጊዜ፣ ከ8 ቀን በፊት የክብር ዘበኛ መረጃ ሠራተኞች በሻምበል ኃይሉ አዴሳ ኃላፊነት ለውስጥ ጥበቃ ተብሎ የገቡት፣ ከአሽከሮች መካከል እደርጐቹ ላይ አደጋ እንዳይጣል ቁጥጥራቸው ፍፁም ሌላ ነበር፡፡ ከውጭ ደግሞ ዙሪያውን ከፎቅ ሆኖ እንዳይተኮስባቸው መሳሪያዎቻቸውን ወደላይ አድርገው ይጠብቁ ነበር፡፡
ደርጐቹም ገብተው ጃንሆይን እስከተገናኙ ድረስ የነበራቸው መረበሽ ከባድ ነበር፡፡ ከቢሮ ተጠርተው ሲገቡ እያንዳንዳቸው ሙሉ ትጥቅ ነበራቸው፡፡ ፊልም አንሺዎች፣ ፎቶግራፍ አንሺዎች፣ የድምጽ መቅረጫ የያዙ ጋዜጠኞች፣ ሪፖርተሮችና የወታደር ጋዜጠኞች ጭምር አብረው ገብተዋል፡፡ ከጋዜጠኞች የማውቃቸው አቶ ማዕረጉ በዛብህ፣ አቶ ደበበ እሸቱ (የድምጽ መቅረጫ) የያዘ፣ አቶ ተፈሪ ብዙአየሁ (የቴሌቪዥን ፊልም አንሺ) መብራት የሚያበራውን ስሙን አላውቀውም እንጂ ለዚሁ ሥራ ብዙ ጊዜ ይመጣል፡፡ ሻለቃውም አዋጁን አነበበ፡፡ በሚያነብበት ጊዜ ኡዚውን ከደረቱ ላይ አንግቶ ነው፡፡ አዋጁ ሲነበብ ግርማዊነታቸው በጽሞና በደንብ ሁነው ያዳምጡ ነበረ፡፡ ከዘወትሩ አሁንም ምንም ለውጥ አላሳዩም ነበር፡፡
አዋጁን አንብቦ ሲጨርስ፣ ግርማዊነታቸው የተገለለ ቦታ እንደተዘጋጀላቸው ስለሆነ ከልዕልት ተናኘ ጋር እንዲቀመጡ ስለተወሰነ አብረዋቸው እንዲሄዱ ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም ተዝናንተው ተቀመጡና “እኛ ለሀገራችን በጦርነትም ሆነ በሰላም ጊዜ ሠርተንላታል፡፡ እናንተም ይህን ጠንቅቃችሁ ታውቁታላችሁ” ብለው ንግግራቸውን ሳይጨርሱ፣ ወታደሮቹ አንድ ጊዜ ግር ግር አሉና ጋዜጠኞቹን በሙሉ አስወጡዋቸው፡፡ ጋዜጠኞቹ ከወጡ በኋላ ንግግራቸውን በእርጋታ በመጀመር፣ “መጀመሪያ የጦር ኃይላችንን በዘመናዊ መልክ ስናዘጋጅ፣ ይህ አሁን የደረሰው የመሳሰሉ ነገሮች እንደሚደርሱ አስቀድመን የተገነዘብነው ስለሆነ ለኛ አዲስ አይደለም፡፡ ነገር ግን የወታደር ተግባሩ ጠረፍን ከአጥቂ ጠላት መጠበቅ ሲሆን፤ አሁን እናንተ በከተማ ተቀምጣችሁ አላማችሁን በመርሳት የምታደርጉት ትክክል አይደለም፡፡
“ወታደር ለጠረፍ እንጂ መቼ ለከተማ” አሉዋቸውና አንዳንዶቹን እየጠሩ መጠየቅ ጀመሩ፡፡ አንዱን የአየር ኃይል ባልደረባ “ና” ብለው፤ “ዕድሜህ ስንት ነው? አገልግሎትህስ?” እያሉ ሲጠይቁ፣ እኛንም በዚያ አካባቢ የነበርነውን አባረሩን፡፡
ወደዚያው አድሚራል እስክንድር ከእህቶቻቸው ጋር ፎቅ ላይ ስለነበሩ አስጠሩኝና ወጣሁ፡፡ እርሳቸውም ጀ/ፍሬሰንበት ከአጠገባቸው በምንም ዓይነት እንዳይለይ ንገረው ብለውኝ እሺ አልኳቸውና ቆምኩ፡፡ ወደዚያው ወደ መኝታ ቤት ከወሰኔ ጋር ገብተን፣ በመስኮት ቁልቁል ስናይ አንዲት ቮልስዋገን መኪና ስትቀርብ አየንና ሊወስዱዋቸው ነው ብለን ሮጠን ስንወርድ፣ አድሚራል ተጠርተው ወርደው ጃንሆይም ሲወጡ ደረስን፡፡ ወደዚያው ጃንሆይ የሚረዳዎት አሽከር ስለሚያስፈልግ፣ እርስዎ ደስ የሚልዎትንና የሚረዳዎትን ይምረጡ ሲሉ፣ እርሳቸውም “ወሰኔ ይሁንልኝ” አሉና መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ሲወጡም ዘወትር ለሽርሽር እንደሚወጡ ነበር፡፡
ወታደሮቹም ከግራና ቀኝ እንዲሁም ከኋላ አጅበዋቸው ነበር፡፡ ውጭ እንደወጡም የሹፌራቸው የጀ/ሉሉ ቮክስዋገን ቆማ ስለነበር፣ አጠገቧ ሲደርሱ ግራ ገባቸውና ቆሙ፡፡ ወደዚያው በሩ ሲከፈትላቸው ስለገባቸው ገቡ፡፡ በዚህ ጊዜ ውሾቻቸው አብረው ገቡ፡፡ ጐትተው አስወጡዋቸው፡፡ ከእሸቱ ጋር ጭቅጭቅ ተፈጠረ፡፡ በመጨረሻ ውሾቹን ታቅፎ ወደ ውስጥ አስገባቸው፡፡ በማግስቱ ዶክተር ግርማ መጥቶ ወሰዳቸው፡፡ በፊትም የሚያክማቸውና ሲያማቸውም እርሱ ቤት ነበር የሚሄዱት፡፡ እርሳቸው በቮክስዋገንዋ ሲሄዱ፣ አድሚራልን ደግሞ በትልቁዋ ኩምቢ ቮክስዋገን (የፖሊስ ናት) አስገብተው ወሰዱዋቸው፡፡ እኛም ተመልሰን እኔና ወሰኔ ዕቃ መክተት ጀመርን፡፡ ለኛ የመሰለን፣ የወሰዱዋቸው ግርማዊት ቪላ/የልዕልት ቤት/ ወይም ልዑል መኰንን ቤት እንጂ 4ኛ ክፍለ ጦር አልመሰለንም፡፡ ምክንያቱም የወጡት በ2ኛ በር ስለነበረ ነው፡፡ እኛም የሚያስፈልገውን ልብስ አዘጋጀን፡፡ ብዙውንም አውጥተን ከተትን፡፡ በዚህ ጊዜ የተቀሩት ቁጭ ብለው ይተክዙ ነበረ፡፡ አንዳንድ የሴት አሽከሮች ለዚያውም ድሆቹ ከሚያለቅሱ በስተቀር ከሌሎቹ አንድም የሚያለቅስ አልነበረም፡፡

Image

በዚያ አካባቢም የተገኙት የበሉት ሳይሆኑ ድሆቹ ነበሩ፡፡ የበሉትማ ገና ዱሮ ወጥተው ዙሪያውን ያንዣብባሉ፡፡ በ5፡30 ሌሎች የደርግ አባሎች መጡና በጀ/ወርቁ የክብር ዘበኛ ተጠባባቂ አዛዥ አማካኝነት ከመኝታ ቤት ገቡ፡፡ ወደዚያው ቤቱንና ዕቃውን እየተመለከቱ፣ ግማሾቹ “መታሸግ አለበት” ሲሉ፣ ግማሾቹ ደግሞ የተለየ ሃሳብ ሲያቀርቡ፣ እኔና ወሰኔ ጀ/ወርቁን ዕቃ መክተት ያስፈልግ እንደሆነ ፈቃድ ጠየቅናቸው፡፡ እርሳቸውም “የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ቶሎ ቶሎ አውጡ” ብለው ፈቀዱልንና ጨርሰን አወጣንና ከተትን፡፡ እነርሱም ቤቱ በመታሸጉ ተስማሙና ታሸገ፡፡ ለጃንሆይ የሚያስፈልግ ዕቃ ሲኖር ከእኛ ዘንድ ሁለት ወይም ሦስት ሰው እየመጣ፣ ከአሽከሮቹ ጋር ከፍተው ዕቃው ከወጣ በኋላ እንደገና ይታሸጋል ብለው ተስማሙና አሸጉት፡፡
ከመኝታ ቤት የደርጉ አባሎች በገቡ ጊዜ አብዛኛዎቹ የሐዘን ስሜት ነበራቸው፡፡ በተለይም አንድ የጦር ሠራዊት ባሻ እንባው መጥቶ ግጥም ሲልበት፣ እንዳይታይ ዞር ብሎ እንባውን ሲጠርግ አይቻለሁ፡፡ የዕቃውንም መመሰቃቀል አይተው፣ “ይኸ ሳይነካ እንዳለ መሆን አለበት” በማለት ምንም ሳይነኩ ወጡ፡፡ ከዚያም ወደ ሳሎንና ገበታ ቤት ሄደው ዕቃውን እያዩ ሲያሽጉ፣ በ6፡45 ሌሎች የደርጉ አባሎች አቶ መንበረ ወልደማርያምን ይዘው መጡ፡፡ ከዚያም በፊት መጥተው ያሽጉ የነበሩትን የደርጉ አባሎች ጠርተው እሽጉን አስከፍተው ከመኝታ ቤት ገቡ፡፡ ከዚያም ትልቁን የገንዘብ መያዣ ቦርሳ ከፍተው፣ ከውስጡ ያለውን ብርና ልዩ ልዩ ዶክሜንት ማየት ጀመሩ፡፡ ታዲያ የቦርሳው ቁልፍ ከጃንሆይ ቀለበት ሥር ነበርና ቀለበቱን አምጥተው ነው የከፈቱት፡፡ ከአንድ ፊት ያለው ግን በቁጥር የሚከፈት ስለሆነና ስለላላወቁት ግማሾቹ “ይቀደድ” ሲሉ፣ አንድ መኰንን ግን “ይህ መቀደድ አይገባውም፣ ለታሪክ መቀመጥ አለበት” ስላለ፣ በመፈልቀቅ በእጃቸው እየገቡ በጐን በኩል አወጡ፡፡ በ7፡10 ሰዓት ልብሱና ምግቡ ጃንሆይ ወደአሉበት ቦታ ሄደ፡፡ …ለዘመን መለወጫ በዓል የተዘጋጀው ግብር የቀረበው ለደርጉ አባሎች ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ እነዚያ ሲያማቱና ለዚህ ውድቀት ያበቁዋቸው፣ ሲዘርፉ የነበሩት አንደኛቸውም አልነበሩ፡፡ እዚያ ተኩራምተው ሲያለቅሱና ሲያዝኑ የነበሩት ምንም ያልተደረገላቸው ድሆቹ ብቻ ነበሩ፡፡ የጦር ሠራዊት ባልደረባ፣ ወታደር፣ ሹፌር፣ መጡ፡፡ ከዚያም እኔ ዘንድ መጥተው ምንም የሄደ “ዕቃ ስለሌለ ልንወስድ ነው የመጣነው፡፡ በተለይም የሚያርፉበት አልጋ ስለሌለ ቶሎ ቢሰጠን” ብለው ጠየቁኝ፡፡ እኔም “አቶ ጥላሁን እኮ ገና ከሰዓት በፊት ሄዶአል” ብለውኛል፤ ምናልባት አላስገባ ብለዋቸው እንደሆነ ብላቸው “የለም ውሸት ነው!” አለኝ፡፡
በተለይም የ10 አለቃው በጣም በማዘን “እስከ አሁን እኮ ከአንዲት ትንሽ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ነው ያሉት፤ ምነው እንደው የሚያስብ ሰውም የለ እንዴ?” አለኝ፡፡ እኔም ወደዚያው ወደ ዕቃ ክፍሉ ያሉትንና የሚያሽጉትን የደርጉ አባሎች ሄጄ ባነጋግራቸው፤ “ለምን እስከአሁን አልሄደላቸውም?” ቢሉኝ ሰው ቸልተኛ ስለሆነ ከእናንተ ዘንድ የሚያስገድድ ይሰጠኝ፡፡ በተለይም የዚህን ሥራ/ፕሮሲጀር/ የሚያውቀው ሻለቃ ሳህሌ ስለሆነ ከአለበት ቦታ ተፈልጐ እንዲወሰድ ብዬ ለአንድ የክብር ዘበኛ ሻለቃ ስነግራቸው፣ እርሳቸውም አንድ መቶ አለቃ ከላይ ግቢ ወጥቶ ለወታደሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥና ዕቃ የሚወስዱ ሰዎች እንዳይቸገሩና በተለይም የሚስቸግሩ ሰዎች እንዳሉ እንዲያስገድዱ ብለው ሰጡኝ፡፡
ግርማዊነታቸው 4ኛ ክፍለ ጦር እንደደረሱ ኪሳቸው ተፈትሾ ብዕር፣ ክራቫት፣ ብራስሌት፣ ቀበቶ… ቀለበታቸውን፣ የአንገት ሐብላቸውን አውልቀው ወሰዱባቸው፡፡ ከዚህም ሌላ የማስታወሻ ደብተራቸውን ጭምር ወሰዱባቸው፡፡
በማስታወሻቸው ላይ ከመያዛቸው ሦስት ቀን በፊት ለአቶ መንበረ 10ሺ ብር ሰጥተው ኖሮ፣ ያን የሰጡትን ገንዘብ በማስታወሻቸው ላይ ጽፈውት ስለተገኘ፣ አቶ መንበረን ከታሰሩበት ቦታ ሄደው ገንዘቡን ለምን እንደወሰዱ ጠይቀው፣ “ለልጆቼ ማሳደጊያ ነው” ሲሉ፤ “አምጡ” ተብለው ያንን 10ሺ ብር መልሰው ለደርጉ አስረከቡ፡፡ ጃንሆይ የገቡባት ክፍል አራት በሦስት ስፋት ያላት ክፍል ስትሆን በውስጧም የነበሩት ሁለት ጥቋቁር የቆዳ ወንበሮች ብቻ ነበሩ፡፡ ክፍሉንና ወንበሮቹን ራሴ አይቻለሁ፡፡ ያን ጊዜ ጊዜ የነበሩት ከበረንዳ ላይ ነበር፡፡ የልዕልት ተናኘወርቅም ቦርሳ እንደዚሁ ተይዞ ከውጭ ቀርቶአል፡፡ በ12 ሰዓት አልጋና ምንጣፍ ስለሄደ ሊነጠፍላቸው ሲል፤ “ምንም አልፈልግም” ብለው ምንጣፉን አስወጥተው ጣሉት፡፡ አልጋው ደግሞ ሁለት ፍራሽ ስለነበረው፣ የላይኛውን ፍራሽ አንሱ ብለው አስነስተው እታችኛው ላይ ተኙ፡፡ ብርድ ልብሳቸውም አንድ ብቻ እንዲሆን አድርገው ከዚያው አደሩ…
=====
“…እኛ እኮ እጃችንን የሰጠነው አውቀን ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንደሚመጣ አስቀድመን የተረዳነው ጉዳይ ነው፡፡ እኛ በሰላም እጃችንን የሰጠነው የህዝቡ ደም እንደራሺያና ፈረንሳይ ሪቮሉሲዮን በከንቱ እንዳይፈስ በማሰብና መከራችንን እኛው እንቀበል በማለት ነው፡፡ የሩሲያንም ሆነ የፈረንሣይን ሪቮሉሲዮን ደህና አድርገን ስለምናውቅ ነው፡፡ ከዚህ በላይ የወታደሩ እንቅስቃሴ ሶሺያሊስት እንደሚሆን አስቀድመን ተገንዝበነዋል፡፡ ስለዚህ ከላይ ባሉት አገሮች የደረሰው እልቂት በእኛም አገር እንዳይደርስ በማሰብ ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ ሲጀመር ይህ በቀጥታ እንደሚመጣ እናውቀው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ያመጣው ስለሆነ መታገል አይቻልም፡፡ የወደፊቱንስ ማን ያውቃል፡፡ ሁሉ በእርሱ እጅ አይደል?”…

Post Reply

Return to “Ethio General .... ኢትዮ ማህበረሰባዊ ርዕሶች”