በአሸባሪዎች ጥቃት የደበዘዘው የአፍሪካ ዋንጫ

እግር ኳስ ፣ አትሌቲክስ ...
Soccer, Premier league, Athletics...
User avatar
girreda
Runner
Runner
Posts: 55
Joined: 01 Oct 2009 12:45
Location: Adama University
Contact:

በአሸባሪዎች ጥቃት የደበዘዘው የአፍሪካ ዋንጫ

Unread post by girreda » 14 Jan 2010 07:58

Image(በኃይሌ ሙሉ)

ባለፈው ሳምንት አርብ በተገንጣይ ታጣቂዎች በተሰነዘረባቸው ጥቃት ሦስት ባልደረቦቻቸውን በሞት ያጡት የቶጐ እግር ኳስ ተጫዋቾች በአንጐላ የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር አቋርጠው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ተጫዋቾቹ በአንጐላ ለመቆየት ፈልገው የነበረ ቢሆንም የቶጐው ፕሬዚዳንት ፍኡር ኛሲምቤ ተጫዋቾቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ያስተላለፉት ትዕዛዝ ተፈጻሚ ሆኗል፡፡

የቶጐ ስፖርት ሚኒስትር በበኩላቸው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የቶጐ ብሔራዊ ቡድን የሚያካሂደውን የጨዋታ ፕሮግራም እንደገና የሚያስተካክል ከሆነ ቡድኑ ወደ አንጐላ ሊመለስ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ቶጐ ለሞቱትና ለቆሰሉት የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኑ አባላት የሦስት ቀን ሃዘን አውጃለች፡፡ የቶጐው እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አምበል ኢማኑኤል አዲባዬር አደጋወን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ "በሞት ላጣናቸው ባልደረቦቻችን ሀዘናችንን መግለጽ አለብን፡፡ ወደ አገራችን የምንሄደውም ይህንን ለመፈጸም ነው፡፡ አርብ እለት በደረሰብን ጥቃት ሁላችንም የሞት አፋፋ ላይ ደርሰን ነው የተመለስነው፡፡ በእለቱ ለቤተሰቦቻችን የመጨረሻ የጽሑፍ መልዕክት ልከናል፡፡ የመጨረሻ ቃል ያልነውን በስልክ ተናግረናል" ብሏል፡፡

የአንጐላው ፕሬዚዳንት ጆስ ኢድዋርድ ዶስ ሳንቶስ በበኩላቸው የአንጐላና የማሊ ብሔራዊ ቡድን ባካሄዱት የአፍሪካ ዋንጫ የመክፈቻ ውድድር ላይ ባደረጉት ንግግር "ሽብርተኞቹ ጥቃት ቢፈጽሙም ካቢንዳ ውድድሩ የሚካሄድባት ከተማ ሆና ትቀጥላለች፤ መፍራት አያስፈልግም" ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ኦሜሌቴ አባሉ እና የሚዲያ ኦፊሰሩ ስታን ኦኮሉ በጥቃቱ የተገደሉ ሲሆን ጀርባው ላይ በሁለት ጥይት የተማታው ተጠባባቂ በረኛው ኮጀቪች አቢላሌ በጆሀንስበርግ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደገለት ይገኛል፡፡ እስካአሁን ድረስም ከኮማ አለመውጣቱን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

የባየር ሊቨርኩስኑ አሲሚዮ ቱሬ የካቢንዳ ተገንጣይ ቡድኖች በቶጐ ብሔራዊ ቡድን ላይ የፈጸሙትን ጥቃት አስመልክቶ ሲናገር "ክስተቱ ዘግናኝ ነበር፡፡ ሹፌሩና ሌሎች ሁለት ሰዎች ከወገብ በላይ በጥይት ሲመቱ የተቀሩት ደግሞ እግሮቻቸውን ተመትተዋል፡፡ ከሞት የተረፉት አሁን ቀዶ ህክምና ተደርጐላቸው ህክምና እየተከታተሉ ነው፡፡ በእኔ ላይ ምንም አደጋ አልደረሰብኝም፤ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይግባውና ከኋላ ወንበር መቀመጤ አትርፎኛል" ብሏል፡፡

በቶጐ ብሔራዊ ቡድን ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ የአንጐላ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችን በስፋት አሰማርቷል፡፡ ነገር ግን እርምጃው አነስተኛና የዘገየ ተደርጐ ተወስዷል፡፡ በቶጐ ብሔራዊ ቡድን ላይ ለደረሰው ጥቃት የአንጐላን መንግሥት ተጠያቂ የሚያደርጉ ዘገባዎች በየቀኑ እየወጡ ነው፡፡

በጫካ የተሸፈነችው ካቢንዳ አብዛኛው የአንጐላ ነዳጅ ዘይት የሚወጣባት አውራጃ ስትሆን በርካታ ተገንጣይ ቡድኖች አወራጃዋን ከአንጐላ ገንጥለው ለማስተዳደር የረጅም ጊዜ ጦርነት አካሂደዋል፡፡ ምንም እንኳን እ.ኤ.አ 2006 በመንግሥትና በተገንጣይ ቡድኖቹ መካከል የሰላም ስምምነት ቢካሄድም አሁንም ድረስ ጥቂት ሸማቂ ቡድኖች አልፎ አልፎ ከመንግሥት ጦር ጋር እንደሚፋለሙ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ ተገንጣይ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በካቢንዳ የሚካሄድ ከሆነ ጥቃት እንደሚሰነዝር ቀደም ብሎ አስጠንቅቆ ነበረ፡፡ የአንጐላ መንግሥት ግን በወቅቱምንም ችግር እንደማይፈጠር በማረጋገጥ የጥቃት ስጋቱን አጣጥሎታል፡፡ ከውድድሩ በፊት መግለጫ የሰጡት የቀድሞው የተገንጣይ ቡድኑ መሪ እና የአሁኑ ሚኒስትር አንቶኒዩ ቤንቶ ቤምቤ "ካቢንዳ በአሁኑ ሰዓት ሰላም የሰፈነባት ቦታ ነች፤ የደህንነት ጉዳይም አያሰጋም፤ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በካቢንዳ መካሄዱ አውራጃዋ ብዙ ጐብኝዎች እንዲያይዋትና ኢንቨስተመንትንም እንድትስብ የሚያደርግ ነው" ብለው ነበር፡፡

ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ግን መግለጫውን የሰጡት ከነበራቸው ጠንካራ እምነት የተነሳ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም "በአፍሪካ ዋንጫ ለመወዳደር ወደ አንጐላ የመጡ ወንድሞቻችን ላይ ይህ አደጋ በመድረሱ በጣም አዝኛለሁ" ብለዋል፡፡

በቶጐ ብሔራዊ ቡድን ላይ የደረሰው ጥቃት እንዴት እንደተፈጸመ ብሔራዊ የሚያጣራ ቡድን አንጐላ ያቋቋመች ሲሆን አማፂ ቡድኖች በሚንቀሳቀሱበትና በአደገኛነቱ የሚታወቀውን የካቢንዳን አውራጀ ብሔራዊ ቡድኑ ለምን በመኪና ለማቋረጥ መረጠ የሚለው ጉዳይም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

የቶጐ ጠቅላይ ሚኒስትር ጊልቤርት ሁዋንግቦ በበኩላቸው የካቢንዳን አካባቢ የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ካፍ ለብሔራዊ ቡድኑ መረጃ አልሰጠም ሲሉ ተችተዋል፡፡ "የፀጥታን ሁኔታ በተመለከተ የራሳችን ጥናት እንድናካሂድ የሚያስችል መረጃ አልደረሰንም" በማለት ጥፋቱ የካፍ መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ የአንጐላ መንግሥትም በአውቶቡስ ወደ ካቢንዳ መሄድ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለምን እዳላሳወቀ ማብራሪያ እንዲሰጠው የቶጐ መንግሥት ጠይቋል፡፡ የአንጐላ ባለሥልጣናት በበኩላቸው የቶጐ ብሔራዊ ቡድን ከኮንጐ ተነስቶ በአውቶቡስ ወደ ካቢንዳ ማምራቱ ያስገረማቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ቶጐ ብሔራዊ ቡድኗን ከአንጐላ የጠራችበትን ምክንያት እንደሚረዳ የገለጸው ካፍ በካቢንዳ የሚካሄዱት ሌሎቹ ስድስቱ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች በተያዘላቸው ፕሮግራም መሰረት እንደሚካሄዱ አስታውቋል፡፡

Post Reply

Return to “Ethio Sport .... ኢትዮ ስፖርት”