Page 1 of 1

ሕወሓት በምርጫ 2007 በትግራይ ክልል ሊሸነፍ እንደሚችል አመነ

Posted: 02 Apr 2014 12:03
by zeru
Image
(ከዚህ ቀደም የአረናን ሕዝባዊ ስብሰባ እንዳይሳተፉ የተከለከሉ የሽሬ ነዋሪዎች – ፎቶ ከአብርሃ ደስታ) – ፎቶ ፋይል
ዓረና ፓርቲ በትግራይ ክልል ወረዳዎች በመዘዋውር ባሰብሰበው መረጃ መሰረት በ2007 በሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ገዥው ፓርቲ የህዝብን ድምፅ ካከበረ ህወሓት በመላው ትግራይ ሙሉ በሙሉ ይሸነፋል። አንድ የህወሓት የስራ አስፈፃሚ አባል (ለግዜው ስሙ ይቅር) በዓዲግራት ከተማ ለተሰበሰቡ ከምስራቃዊ ዞን የተውጣጡ የህወሓት ካድሬዎች “እናንተ በምትፈፅሙት በደል ምክንያት በ2007 ምርጫ እንሸነፋለን። ግን አንዳንድ የምናደርጋቸው ነገሮች ስለሚኖሩ ሙሉ በሙሉ ተስፋ አትቁረጡ። ለራሳችሁ ዕጣ ፈንታ ስትሉ በደንብ ስሩ” ማለቱ ታውቋል። ካድሬዎቹም “በናንተ (የላይኞቹ አመራሮች) ችግር ነው የምንሸነፈው፤ ህዝብ የማይቀበለውን ነገር እንድናሳምን ታስገድዱናላቹ” የሚል መልስ በመስጠታቸው የእርስበርስ ንትርክ መከፈቱ ታውቋል። ከስብሰባው በኋላ ካድሬዎቹ የንትርኩ ነጥቦች ለዓረና አባላት አስረድተዋል።
በዓረና እንቅስቃሴ የሰጉ የህወሓት መሪዎች ህዝብን በገንዘብ መደለል ጀምረዋል። ባሁኑ ግዜ የትግራይ ህዝብ በህወሓቶች በሦስት ደረጃዎች ተከፍሎ ግሬድ ተሰጥቶታል። ግሬድ A, B ና C። ግሬድ “A” ታማኝ የህወሓት ካድሬ፣ ግሬድ “B” መሓል ሰፋሪ፣ ግሬድ “C” ተቃዋሚ (ዓረና)። በዚሁ መሰረት ህወሓትን ለማገልገል ፍቃደኛ የሆነ ሰው (ታማኝ ካድሬ A) ለስብሰባ ይጠራና የማዳበርያን ዕዳ ለመክፈል የሚያግዘው 3000 ብር የውሎ አበል ተብሎ ይሰጠዋል። 3000 ብር ከተቀበለ በኋላ ተቃዋሚዎችን ይታገላል፣ ህወሓት እንዲመረጥ ያግዛል፣ ታማኝ የህወሓት አገልጋይ ይሆናል። ለህወሓት ታማኝ ያልሆነ ለስብሰባ አይጠራም፤ ገንዘብም አይሰጠውም። በ3000 ብር የምርጫ ድምፅ መግዛት ይሉታል እንዲህ ነው። የምርጫ ድምፅ እየተገዛበት ያለ ገንዘብ የህወሓት ሳይሆን በግብር መልክ የተሰበሰበ የመንግስት ገንዘብ ነው። መንግስት ብር አነሰኝ እያለ ግብር እየጨመረ ነጋዴዎች ንግዳቸውን ይዘጋሉ። ህወሓቶች ደግሞ የሰበሰቡትን ገንዘብ ለምርጫ ጅንጀና ይጠቀሙታል።
የትግራይ አርሶአደሮች እንደዚህ በፖለቲካ ታማኝነት በዉሎ አበል መልክ ገንዘብ እየተሰጣቸው የማዳበርያ ዕዳቸውን መክፈል ከቻሉ ጥሩ ነው። ባንዳንድ አከባቢዎች ግን የዉሎ አበሉ መጠን ይለያያል። ለምሳሌ በደቡባዊ ምስራቅ ዞን ለየት ያለ አጋጣሚ ተፈጥሯል። ህወሓቶች በሁሉም ዞኖች እንደሚያደርጉት ሁሉ ታማኝ የተባሉ (ለምርጫ ሊያገለግሉ የሚችሉ) 200 የሳምረ አርሶአደሮች መለመሉ። አርሶአደሮቹ ሲመለመሉ “ለስብሰባ ትሄዳላቹ፣ 3000 ብር አበል ይሰጣችኋል፤ ስለዚህ 3000 ብሩን ለማግኘት በመጪው ሰኔ ላይ ለምትወስዱት ማዳበርያ 1200 ብር አሁን ክፈሉ” ይሏቸዋል። አርሶአደሮቹም 3000 ብሩን ለማግኘት 1200 ብር እንደምንም ብለው ከፈሉ። ከሳምረ ለስብሰባ ተብሎ ወደ ሕዋነ ተወሰዱ፤ ፖለቲካ ተጀነጀኑ። በመጨረሻ እነሱ 3000 ብር እየጠበቁ 640 ብር ብቻ እንደሚሰጣቸው ተነገራቸው። ከ640 ም 600 ው መቆጠብ አለባቹ በሚል ሰበብ በህወሓቶች እጅ ሲቀር 40 ብር ብቻ ለትራንስፖርት ተሰጣቸው። አርሶአደሮቹ አሁን ቅሬታቸው አካፍለውናል።

አዎ! የህዝብ ድምፅ ከተከበረ ዓረና ሙሉ በሙሉ ያሸንፋል። እናም ህወሓቶች በሰለማዊ መንገድ ስልጣን ያስረክባል። የህወሓት ካድሬዎችም መብታቸው ተጠብቆላቸው በሰላም በሀገራቸው ይኖራሉ። ከፈለጉ በመንግስት መስራቤት በሙያቸው ተቀጥረው ይሰራሉ፣ ወይም ህወሓት ተቃዋሚ ፓርቲ አድርገው ለሚቀጥለው ምርጫ ለመወዳደርና ለማሸነፍ ይሞክራሉ። በሰለማዊ መንገድ ስልጣን ለማስረከብ ካልፈለጉ ግን በሃይል እስኪወገዱ ድረስ በስልጣን ይቆያሉ። በሃይል ከተሸነፉ እንደ የደርጎቹ ከሀገር ተጠርገው ይባረራሉ፤ የደርግ ባለስልጣናት ዕጣ ፈንታ ይቀምሳሉ።
ስልጣን ለህዝብ እናስረክብ፤ ሰለማዊ የስልጣን ሽግግር ይኑር። ስልጣን ለህዝብ ካላስረከብን ግን ሌላ ታጣቂ ሃይል ይነጥቀዋል። ከዛ ስልጣን ባላንጣን መምችያ ዱላ ይሆናል። ዱላው ከህዝብ ጋር መሆን አለበት።
==================
ሰላማዊ ሰልፍ በደርግና ህወሓት
“የትግራይ ህዝብ ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱ ከተነፈገ እነሆ 22 ዓመታት አለፉ” ብዬ ለፃፍኩት “ከ22 ዓመታት በፊት ሰለማዊ ሰልፍ ማድረግ ይፈቀድ ነበር እንዴ? በደርግ ግዜስ ሰለማዊ ሰልፍ ይፈቀድ ነበር ማለት ነው?” የሚል ጥያቄ መጣብኝ።
የደርግ ዘመን በትግራይ ክልል የጦርነት ግዜ ነበረ። በጦርነት ግዜ ሰለማዊ ሰልፍ አይፈቀድም። በደርግ ግዜ ሰለማዊ ሰልፍ ማድረግ በህገመንግስት የተደነገገ መብት አልነበረም። በደርግ ዘመን ስርዓት አልነበረም። ደርግ ትግራይን አልተቆጣጠረም ነበር። ግማሹ የትግራይ መሬት በደርግ ወታድሮች ቁጥጥር ሲሆን ግማሹ ደግሞ በህወሓቶች እጅ ነበረ (ሓራ መሬት ትግራይ)። ስለዚህ አንድ መንግስት የዜጎችን መብት ለማስከበር መጀመርያ ስርዓት መመስረት አለበት። በሁሉም አከባቢዎች አስተዳዳራዊ ስራና ቁጥጥር ሊኖረው ይገባል። ደርግ በትግራይ አስተዳዳራዊ ቁጥጥር አልነበረውም። የዜጎችን መብት ለማስከበር ሕገመንግስት መደንገግ አለበት። በደርግ ግዜ ሕገመንግስት አልተደነገገም ነበር ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ደርግ ወታደራዊ መንግስት ነበርና። ወታደራዊ መንግስት ሕግ አያከብርም፤ ስለ ስልጣኑ እንጂ ስለ ህዝብ መብት አይጨነቅም።
ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቱ ተነፈገ ሲል በደርግ ግዜ መብቱ ተከብሮለት ነበር ማለቴ አይደለም። መልእክቱ ህወሓትም ከደርግ እሻላለሁ፣ ደርግን አስወግጄ የህዝብ መብት አስከብራለሁ፣ ነፃነት እፈቅዳለሁ እያለ የትግራይን ህዝብ ድጋፍ አሰባስቦ ቤተመንግስት ከገባ በኋላ ሌላ ደርግ ሆነብን ለማለት ተፈልጎ ነው።
ህወሓት ራሱ ከደርግ ጋር ማወዳደር ቢተው ጥሩ ይመስለኛል። ምክንያቱም በደርግ ግዜኮ (በትግራይ ማለቴ ነው) ስርዓት አልነበረም። የደርግ ዘመንኮ የጦርነት ዘመን ነው የነበረው። ስለዚህ አንድ መንግስትነት ተቆጣጥርያለሁ የሚል ስርዓት ራሱ ከጦርነት ዘመን ጋር እንዴት ያወዳድራል? ህወሓት ራሱ መፈተሽ ያለበት አሁን መስራት ካለበትና መስራት ከሚጠበቅበት አንፃር መሆን አለበት።
አብርሃ ደስታ ከመቀሌ