ኢሕአዴግ ለምን ማኅበረ ቅዱሳንን ማፍረስ ፈለገ?

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

ኢሕአዴግ ለምን ማኅበረ ቅዱሳንን ማፍረስ ፈለገ?

Unread post by zeru » 29 Mar 2014 20:22

ሥርዐቱ በተለይም መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን ለሃይማኖታዊ ተልእኮ የሚጠቀሙ ሓላፊዎችና አማሳኝ የደኅንነት ግለሰቦች አሁን በተያዘው መንገድ ቀጥለው ማኅበረ ቅዱሳንን አላግባብ ወደ መገዳደር ብሎም ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አማሳኝ ግለሰብ ሓላፊዎች ጋራ ተባብረው ወደ ማፍረስ የሚሸጋገሩ ከኾነ ያለምንም ጥርጥር የተቃውሞው ጎራ ይጠናከራል፡፡ ይህም አገሪቱን በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የአውራ ፓርቲ ሥርዐት ለአርባና ኃምሳ ዓመታት እመራለው ለሚለው ገዥው ፓርቲ ግብዓተ መሬት አፋጣኝ ምክንያት ሊኾን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይስማማሉ፡፡
 • በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ሃይማኖታዊና ምጣኔ ሀብታዊ ፍላጎት ያላቸው የገዥው ፓርቲ ባለሥልጣናትና ጥቂት አማሳኝ የደኅንነቱ ሰዎች ተቋሙን አፍርሶና ቤተ ክርስቲያንን በሒደት አዳክሞ በመቆጣጠር አልያም በታትኖ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን ማስረከብ ቀላል እንደኾነ ያስባሉ፡፡ በአንጻሩ ‹‹በምድር ላይ ሊሳኩ ከማይችሉ ነገሮች አንዱ ይኼ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ምኞት ነው፤›› የሚለው አንድ የቀድሞው የማኅበሩ ሥራ አመራር አባል እንደሚያሳስበው፣ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ የማኅበሩ አባላትና ደጋፊዎች፣ ማኅበሩ በግቢ ጉባኤያት አንፆ መስቀል በአንገታቸው አስሮ የሸኛቸው በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ምሩቃን፣ ኦርቶዶክሳውያን ምሁራንና በማኅበሩ ስኬታማና ተጨባጭ አገልግሎት የቤተ ክርስቲያን ፍቅር ያደረባቸው ምእመናን ኹሉ ለዘመናት እየመነዘሩ ማንኛውንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ተግዳሮቶች የሚመክቱበት መንፈሳዊ ኃይል እንዳላቸው በቅጡ መረዳት ያሻል፡፡
 • በርካታ አገራዊ አጀንዳዎች አሉኝ በማለት ሕዝቡን ለሕዳሴ የሚያነሣሣው መንግሥት፣ በተለይም የፀረ አክራሪነቱን ትግል በቅድመ ግንባር እንዲመራ ፖሊቲካዊ ተልእኮ የተሰጠው አካልና ሓላፊዎቹ፣ መካሪ እንደሌለው የእብድ ሥራ ከመሥራታቸውና እጃቸውን ወደ ብልሽት ከመዘርጋታቸው በፊት ነገሮችን በርጋታ ማጤንና በግልጽ ውይይት ማመን ይበጃቸዋል፡፡(ዕንቊ፤ ቅጽ ፮ ቁጥር ፻፲፬፤ መጋቢት ፳፻፮ ዓ.ም.)
  ከሰሞኑ ኢሕአዴግ መራሹ ግብረ ኃይል ማኅበረ ቅዱሳንን የማፍረስ እንቅስቃሴውን ከየትኛውም ጊዜ በባሰ አጠናከሮ መቀጠሉ እየተደመጠ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐቀኛና ዓይናማ አበው ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ዘንድ ዐቃቤ ሃይማኖት ኾኖ የሚታየውና በብዙዎች ምሁራን ዘንድ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምሁራን ክንፍ (academic wing) መኾኑ የሚታመነው ማኅበረ ቅዱሳን የገዥው ፓርቲ ጥቃት ሰላባ መኾኑ አይቀሬነት እውን እየኾነ መምጣቱ ብዙዎችን እያሳሰበ ነው፡፡
  በተለይ ጥቃቱ የማኅበሩ የአስተሳሰብ፣ የመርሕና የስትራተጂ ርትዓተ አእምሮ የኾኑ አመራርና አባላቱ ላይ ማነጣጠሩ ርምጃው ደጅ ላይ ስለመኾኑ ማረጋገጫ ተደርጎ እየተወሰደ ነው፡፡ በኢ.ቴቪ ይዘጋጃል ተብሎ የተነገረውም ዶኩመንተሪ የዚሁ ጥቃት መንገድ ጥርጊያ ተደርጐ መታየት አለበት ይላሉ፤ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር፡፡
  ያልተሳካው ሙከራ!
  እኚህ ምሁር ለዕንቁ መጽሔት እንደገለጹት፣ ሥርዐቱ ማኅበረ ቅዱሳን የማፍረስ አዝማሚያ ማሳየት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ በተለይም በአባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል፣ በንቡረእድ ኤልያስ አብርሃ፣ በሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም የውንጀላ ጽሑፍ አቅራቢነት፤ በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ በነበሩት አቶ ኣባይ ፀሐዬና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስተር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም አቅጣጫ ሰጪነትና ተሳታፊነት መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም የተካሔደው የውንጀላ ስብሰባ ማኅበረ ቅዱሳንን የማፍረስ እንቅስቃሴ ይፋዊ ጅማሮ እንደነበረ የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው፡፡
  በአምስተኛው ዘመነ ፕትርክና መገባደጃ መንግሥታዊ ሥርዐቱ ይኹን ቤተ ክህነቱ የጥፋት እጁ ኾነው ያገለግላሉ የሚባሉት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃና አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ማኅበሩን እንዲዘጉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም ‹‹ፓትርያርኩ የእነርሱን የመጨረሻ ሕልም እውን ለማድረግ ሳይፈቅዱ ላይመለሱ ሔዱ፤›› የሚሉት አንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባል፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ግን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በኻያ ዓመታት ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያልፈጸሙትን ግፍ አንደኛ ዘመነ ፕትርከናቸውን እንኳ ሳያከብሩ ፈጸሙ ይላሉ፡፡
  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የገዥው ፓርቲና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የዘወትር የጥፋት ግንባር አባላትን ግፊት እያለ ማኅበሩን ለመዝጋት ያልደፈሩት፣ ለማኅበሩ በጎ አመለካከት ስላላቸው ወይም በማኅበሩ አገልግሎት ፍቅር ስለወደቁ ሳይኾን ‹‹ማኅበሩን መንካት የሚያስከፍላቸውን ዋጋ ስላሰሉት ነው፤›› ይላሉ አንድ ሊቀ ጳጳስ፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የሥርዐቱን ተልእኮ ለማስፈጸም በሚል የጀመሩት ማኅበረ ቅዱሳንን የማፍረስ እንቀስቃሴ መተባበር፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ውስጥ ከመክተቱም በላይ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው በቅጡ የተረዱ አይመስሉም፤›› ሲሉ እኚኹ ሊቀ ጳጳስ ለዕንቁ መጽሔት ገልጸዋል፡፡
  አዲሱ መግፍኤ ነገር
  ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ቅዱስ ፓትርያርኩን ይኹን በዙሪያቸው የተሰበሰቡትን አማሳኞች ተጠቅሞ ማኅበሩን ለማፍረስ ለምን ፈለገ? ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ አንድ ምሁር፣ ማኅበረ ቅዱሳን ብዙኃን ጳጳሳትን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ምሁራን፣ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችንና ምእመናንን በዙሪያው ለማሰለፍ የሚያስችለው ርእይ፣ ዓላማና አቅም እንዳለው በተግባርም እያሰለፈ ያለ ማኅበር መኾኑን በማስገንዘብ ይጀምራሉ፡፡
  እኚህ ምሁር ማኅበረ ቅዱሳን የቆመለት የአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልማትና ዕድገት አቅጣጫ ጥቅማቸውን በላቀ ደረጃ የሚያስጠብቅላቸው የመኖራቸውን ያህል የኘሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ፣ ብልሹ አሠራርና ተቋማዊ ቀውስ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅላቸው መኖራቸውንም ይጠቅሳሉ፤ በትይዩም ሥርዐቱ የእነዚህ ተጠቃሚ በመኾኑ የማኅበረ ቅዱሳንን መኖር አይፈልግም ይላሉ፤ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማዳከም ወይም ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት ያልተሳካለት ኢሕአዴግ ማኅበሩን ለማፍረስ የመምረጡ አንድ መንሥኤ ይህ ሊኾን እንደሚችልም ያስረዳሉ፡፡
  ዘመናዊ ትምህርት የቀሰሙ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምሁራዊ መለዮ የኾነው የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የጎሳ ይኹን የቤተ ሰብእ ማንነት ሳይለያያቸው ኹሉም በቤተ ክርስቲያንና በሀገር ፍቅር እሳት የሚቃጠሉ፣ አገራቸውና ቤተ ክርስቲያናቸው ሌሎች አገሮችና አኀት አብያተ ክርስቲያናት ከደረሱበት የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ለማድረስ በጎ ፍላጎትና ምኞት የሞላባቸው ናቸው የሚሉት እኚህ ምሁር፣ ገዥው ፓርቲ ማኅበሩን ለማፍረስ ቆርጦ የተነሣበት ሁለተኛው ምክንያት ማኅበሩና መላው አባላቱ ሀገራዊ ብሔርተኝነትን ማቀንቀናቸው ነው ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሥርዐቱ በአቋም ከሚያራምደው የዘውግ ብሔርተኝነት ጋር በእጅጉ ይቃረናል፡፡ በዚህ የተነሣ ማኅበሩ የሥርዐቱ የፕሮፓጋንዳ ጥቃት ሰለባ ኾኗል ይላሉ፡፡
  ማኅበረ ቅዱሳን በእግዚአብሔር ፈቃድና ጥበቃ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ ላለፉት ኻያ ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ሥርዐት፣ ትውፊትና ታሪክ ተጠብቆ እንዲቆይ፤ የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ መምህራንና ደቀ መዘሙርቱ ያሉበት አስከፊ የድህነት ኹኔታ በማጥናት ህልውናቸውን ከሚፈታተነው ችግር ተላቀው፣ በራሳቸው በመተማመን የቤተ ክርስቲያኒቱ የዕውቀት ማእከልነታቸው ጠብቀው ዘመን እንዲሻገሩ፤ ገዳማትና አድባራት በዘላቂ ልማት ተጠቃሚ ኾነው በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉና በአገሪቱ ልማት ተሳታፊና በቅድመ ግንባር አርኣያ እንዲኾኑ በሞያ፣ በገንዘብና በጉልበት ተግባራዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አንድ የቤተ ክህነቱ ከፍተኛ የሥራ ሓላፊ ያስረዳሉ፡፡
  እኚኹ ከፍተኛ የሥራ ሓላፊ ሦስተኛው ምክንያት፣ በመንግሥት የፀረ አክራሪነት ትግል ሽፋን መንግሥታዊ ሥልጣናቸው ተጠቅመው ሃይማኖታዊ ፍላጎታቸውን ማኅበረ ቅዱሳንን በመቅበር ለማሳካት ደፋ ቀና የሚሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ከቤተ ክህነቱ አማሳኞች ጋር ጥብቅ የዓላማና የጥቅም ቁርኝት የፈጠሩ የደኅንነት ሰዎች በጋራ መንግሥትን በማሳሳትና የፕሮፓጋንዳ አቅጣጫውን በመቃኘት የፈጠሩት የሐስት ክሥ ውጤት ነው፤ ብለዋል፡፡
  የሥርዐቱ ስውር እጆች
  የማኅበሩን ተቋማዊ እንቅስቃሴ እንዲገደብና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምንም ዓይነት የምሁራን ንቁ ተሳትፎ እንዳይኖር የሚፈልጉት እኒኹ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና አማሳኝ የደኅንነት ሰዎች ብቻ አይደሉም የሚሉት የቤተ ክህነቱ ከፍተኛ የሥራ ሓላፊ፣ በራሷ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅሮች ውስጥ ሓላፊነት ይዘው በስውር ቤተ ክርስቲያኒቱን ለሚያጠፉ አካላት የማይታይ እጅ ኾነው በመሥራት ላይ ያሉ ግለሰቦችንና ቡድኖችንም እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን መቅበር፣ በመቃብሩም ላይ እያላገጡ መቆም፣ ከዚያም የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነትና ህልውና ለአደጋ አጋልጦ የማትሰማ የማትለማ የእነርሱ ጥገኛና የርካሽ ዓላማቸው መሣርያ ማድረግ ዋነኛ ተልእኳቸው ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ለዕንቁ መጽሔት ሰጥተዋል፡፡
  ቅዱስ ሲኖዶስ በመተዳደርያ ደንብ ቆጥሩና ስፍሮ በሰጠው ተልእኮ መሠረት ማኅበሩ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣ በሥነ ምግባር እንዲታነጹ፣ በተሰማሩበት ሓላፊነት ኹሉ ሀገራዊ ሓላፊነት እንዲሰማቸው፣ የብዙ ታሪክና ቅርስ ባለቤት የኾነችውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ምቹ ጊዜ ጠብቀው ሊያጠፏት ካሰፈሰፉ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን እንድትጠበቅ የሚሰጠውን አገልግሎት በበጎ የማይመለከቱት እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ፓትርያርኩን ጨምሮ የሥርዐቱ ቋሚ ጉዳይ አስፈጻሚ የኾኑ ጥቂት ጳጳሳትም ማኅበሩን በማፍረስ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳሉ ይገለጻል፡፡
  ማኅበረ ቅዱሳን በኻያ አንድ ዓመታት ታሪኩ የሠራው ሥራ ምሁራን አባላቱ በመዋቅራዊ አሠራር ብቻ ሳይወሰኑ በተናጠልም አፅራረ ቤተ ክርስቲያንን ለመቋቋም፣ በስውርና በግልጽ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የሚፈጸሙ ደባዎችን በማጋለጥ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑንም በአስተውሎትና በመረጃ በታገዘ መንገድ በማንቃት ሰፊ መሠረት ያለው ማኅበራዊ – መንፈሳዊ አቅምና እሴት ፈጥሯል፡፡
  በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ሃይማኖታዊና ምጣኔ ሀብታዊ ፍላጎት ያላቸው የገዥው ፓርቲ ባለሥልጣናትና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አማሳኝ ግለሰብ ሓላፊዎች ጋራ የዓላማና ጥቅም ቁርኝት የፈጠሩ ጥቂት የደኅንነቱ ሰዎች ተቋሙን በማፍረስ ቤተ ክርስቲያንን በሒደት አዳክሞ በመቆጣጠር አልያም በታትኖ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን ማስረከብ ቀላል እንደኾነ ያስባሉ፡፡
  ይኹን እንጂ ‹‹በምድር ላይ ሊኾኑ ከማይችሉ ነገሮች አንዱ ይኼ የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ምኞት ነው፤›› የሚለው አንድ የቀድሞው የማኅበሩ ሥራ አመራር አባል እንደሚያሳስበው፣ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ የማኅበሩ አባላትና ደጋፊዎች፣ ማኅበሩ በግቢ ጉባኤያት አንፆ መስቀል በአንገታቸው አስሮ የሸኛቸው በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ምሩቃን፣ ኦርቶዶክሳውያን ምሁራንና በማኅበሩ ስኬታማና ተጨባጭ አገልግሎት የቤተ ክርስቲያን ፍቅር ያደረባቸው ምእመናን ኹሉ ለዘመናት እየመነዘሩ ማንኛውንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ተግዳሮቶች የሚመክቱበት መንፈሳዊ ኃይል እንዳላቸው በቅጡ መረዳት ያሻል፡፡
  መካሪ የሌለው መንግሥት?
  ሥርዐቱ በተለይም መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን ለሃይማኖታዊ ተልእኮ የሚጠቀሙ ሓላፊዎችና አማሳኝ የደኅንነት ግለሰቦች አሁን በተያዘው መንገድ ቀጥለው ማኅበረ ቅዱሳንን አላግባብ ወደ መገዳደር ብሎም ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አማሳኝ ግለሰብ ሓላፊዎች ጋራ ተባብረው ወደ ማፍረስ የሚሸጋገሩ ከኾነ ያለምንም ጥርጥር የተቃውሞው ጎራ ይጠናከራል፡፡ ይህም አገሪቱን በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የአውራ ፓርቲ ሥርዐት ለአርባና ኃምሳ ዓመታት እመራለው ለሚለው ገዥው ፓርቲ ግብዓተ መሬት አፋጣኝ ምክንያት ሊኾን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይስማማሉ፡፡
  ከዚህም ባሻገር ማኅበሩ ትውልዱ በሃይማኖታዊ ዕውቀት የታጠቀ፣ ቤተ ክርስቲያኑን ያወቀ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን የተገነዘበና በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ ብቁ ዜጋ እንዲኾን የተጫወተውን በጎ ሚና የሚገነዘበው ዜጋ ‹‹መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ደምሮ ማየቱ አይቀሬ ነው፤›› የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ ከእስልምናው የተቃውሞ ጎራ ጋር ትይዩ የኾነና ከቁጥጥር ውጭ የኾነ መቧደን የሚፈጥር ቀውስ ሊቀሰቅስ ይችላል ይላሉ፡፡
  ስለዚህም በርካታ አገራዊ አጀንዳዎች አሉኝ በማለት ሕዝቡን ለሕዳሴ የሚያነሣሣው መንግሥት፣ በተለይም የፀረ አክራሪነቱን ትግል በቅድመ ግንባር እንዲመራ ፖሊቲካዊ ተልእኮ የተሰጠው አካልና ሓላፊዎቹ፣ መካሪ እንደሌለው የእብድ ሥራ ከመሥራታቸውና እጃቸውን ወደ ብልሽት ከመዘርጋታቸው በፊት ነገሮችን በርጋታ ማጤንና በግልጽ ውይይት ማመን ይበጃቸዋል የሚለውን ምክር የሚጋሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”