ደቡብ ሱዳን እና አዳጋቹ የሰላም ድርድር

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

ደቡብ ሱዳን እና አዳጋቹ የሰላም ድርድር

Unread post by zeru » 29 Mar 2014 20:14

Image
በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት የሚመራው የመንግሥቱ ጦር እና የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ሪየክ ማቸርን በሚደግፉት ታጣቂ ኃይላት መካከል በሚካሄደው ውጊያ ሰበብ ሀገሪቱ ለምትገኝበት ውዝግብ መፍትሔ ለማፈላለግ የተጀመረው ጥረት ችግር እንደገጠመው ይገኛል።
የደቡብ ሱዳን መንግሥት ጦር እና በአንፃሩ በሚንቀሳቀሱት ዓማፅያን መካከል ባለፈው ታህሳስ ወር የተጀመረው ውጊያ በወቅቱም እንደቀጠለ ነው። በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት እና በቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ሪየክ ማቸር ደጋፊዎች መካከል ፣ ምንም እንኳን ባለፈው ጥር ወር የተኩስ አቁም ደንብ ስምምነት ቢፈረምም፣ በወቅቱ እየተካሄደ ስላለው ውጊያ በአሁኑ ጊዜ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ቴሌቪዥን በሰፊው ዘገባ ያቀርባል። የጦሩ ቃል አቀባይ ፊሊፕ አግዌር እንደገለጹት፣ የመንግሥቱ ጦር በዚሁ ውጊያ ሰሞኑን ወሳኝ ድል ተቀዳጅቶዋል።
« የመንግሥቱ ጦር በነዳጅ ዘይት በታደለው የአፐር ናይል ግዛት የምትገኘዋን የማላካልን ከተማ ከዓማፅያኑ አስለቅቋል። »
ይህ አሁን በደቡብ ሱዳን መንግሥት እና ባማፅያኑ ተወካዮች መካከል በአዲስ አበባ እንደገና በተጀመረው ድርድር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እናዳያሳርፍ እና ድርድሩ እንዳይቋረጥ ታዛቢዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል። በዓማፅያኑ ሰበብ ድርድሩ ከከሸፈ የመንግሥቱ ጦር በአንፃራቸው ጠንካራ ርምጃ እንደሚወስድ የደቡብ ሱዳን ማስታወቂያ ሚንስትር ማይክል ማክዌይ አስጠንቅቀዋል።
« ዓማፅያኑ በሽሽት ላይ ናቸው፤ በሄዱበት ተከትለን እናሳድዳቸዋለን። እና ይኸው ውዝግብ በጊዜ እልባት ካለተደረገለት በጦሩ ግንባር ላይ መፍትሔ እናስገኝለታለን። ሁኔታው እንዲህ ከቀጠለ የተኩስ አቁም ደንብ ሊደረስ አይችልም፤ የተኩስ አቁም ካልተደረገ ደግሞ ዓማፅያኑ እንደገና እንዲያጠቁን ዕድል አንሰጣቸውም። እንደሚታወሰው፣ የተኩስ አቁሙን ደንብ በመጣስ የማላካልን ከተማ የያዙት ድርድሩን እናካሂድ በነበርንበት ጊዜ ነበር። ይህ ዓይነት ድርጊት እንደገና እንዲፈፀም ዕድል አንሰጥም። እና አንገታቸውን ይዘን እና የገቡበት ገብተን ጠንካራ ርምጃ እንወስድባቸዋለን። »
የማስታወቂያ ሚንስትር ማይክል ማክዌይ ይህን ይበሉ እንጂ። መንግሥታቸው ከታጣቁ ኃይላት ጋ በጠቅላላ በድርድር የተኩስ አቁም ደንብ ለመድረስ አሁንም ዝግጁ መሆኑን በግልጽ አመልክተዋል። ይሁንና፣ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖችን ለማስታረቅ ጥረት የጀመረው የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን፣ በምሕፃሩ ኢጋድ በአዲስ አበባ አሁን እየተካሄደ ያለው ድርድር ሁሉን የሀገሪቱን የህብረተሰብ ክፍል የሚያቅፍ እንዲሆን ያቀረበውን ሀሳብ ማክዌይ ውድቅ አድርገውታል።
« ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ የሰላም ድርድር ይኖራል። ይህ ድርድር ደቡብ ሱዳን ውስጥ ይካሄዳል። ድርድሩንም ራሷ የደቡብ ሱዳን ሬፓብሊክ ከኢጋድ ጋ በመተባበር ታዘጋጀዋለች። በአሁኑ ጊዜ ግን ከዓማፅያኑ ጋ እየተደራደርን ያለነው ለደቡቡ ሰላም ለማውረድ እና ሁሉን አቀፉን ብሔራዊ የሰላም ድርድር ለማካሄድ የሚያስችለውን ሁኔታ ለመፍጠር ነው። »
በመዲናይቱ ጁባ የሚገኘው እና በደቡብ ሱዳን ሥርዓተ ዴሞክራሲ የማነቃቃት ዓላማ ይዞ የተነሳው ተቋም አማካሪ ንህያል ቲትማሜር እንደሚሉት፣ ብዙዎቹ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ግን ኢጋድ አሁን የተጀመረው ድርድር በሀገሪቱ ችግሮች ላይ እና በወደፊቱ ዕጣዋም ላይ እንዲወያይ ያቀረበውን ሀሳብ ደግፈውታል።
« በመጀመሪያ የሰላሙ ድርድር ሁሉን አቀፍ እንዲሆን እንፈልጋለን። የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሁኑ የታጠቁ ቡድኖች ሁሉም በዚሁ ሂደት ውስጥ መጠቃለል መቻል አለባቸው። ተቀናቃኞቹ ወገኖች በዋነኛ ጉዳዮች ላይ፣ ለምሳሌ ፣ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻሉ ጥያቄ ላይ ፣ በደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ ከተገረሠሠ በኋላ የታየው ዓይነት የእርቀ ሰላም ሂደት መጀመር እና መተማመን ሊፈጠር በሚችልበት ጉዳዮች ላይ መውያየት አለባቸው። በሀገሪቱ የግፍ ተግባር የፈፀሙ ሰዎችም ለዚሁ ተግባራቸው በኃላፊነት ሊጠየቁ ይገባል። »
ለደቡብ ሱዳን ውዝግብ መፍትሔ የማፈላለጉ ሂደት ረጅም እና አዳጋች ነው ብለው እንደሚያስቡ ነው « ሲቲዘን » የተባለው ትልቁ የደቡብ ሱዳን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ዕለታዊ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ኒህያል ቦልም የገለጹት።
« ኢጋድ ያቀረበው ሀሳብ ለውዝግቡ መፍትሔ ያስገኛል ብየ አላስብም፤፣ ምክንያቱም ሽምግልናውን የጀመረው በአንድ ፓርቲ ብቻ ተጋብዞ ነው ። ዓማፅያኑ አልተጠየቁም። የዩጋንዳ ጦርም ወደ ደቡብ ሱዳን የገቡት በሀገሪቱ መንግሥት ተጋብዘው ነው። በመጨረሻም የደቡብ ሱዳን መንግሥት ነው ወደ አፍሪቃ ህብረት በመሄድ የኢጋድ ጦር ኃይል እንዲላክለት የጠየቀው። ስለዚህ ፣ እንደማስበው፣ ሂደቱ ቀላል አይሆንም። »
ቢያንስ እአአ ከ 2012 ዓም የፀደይ ወራት ወዲህ በገዢው የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ፣ በምህፃሩ፣ በ «ኤስ ፒ ኤል ኤም » ውስጥ የሚታየው የሥልጣን ሽኩቻ እንደሚባባስ ነበር ቦል የገመቱት። በዚህም የተነሳ የ «ኤስ ፒ ኤል ኤም » አመራር እአአ ባለፈው ታህሳስ 15፣ 2013 ዓም ጉባዔውን ካበቃ በኋላ በተቀናቃኞቹ መካከል ውጊያ መጀመሩ አላስገረማቸውም። ይሁንና፣ አሁን የቀጠለው የኃይል ተግባር ባፋጣኝ እንዲያበቃ እና ስለመሠረታዊው የሀገሪቱ ችግሮች ውይይት መደረግ እንዳለበት ነው ቦል ያሳሰቡት። « ሀገሪቱ መፍትሔ ልታፈላልግለት የሚገባ አንድ ችግር ብቻ አይደለም ያላት፣ ሊመከርባቸው የሚገቡ ከአስተዳደር ጋ የተያያዙ ብዙ ጉዳዮች አሉ። ችግሩ የርዕዮተ ዓለም ጦርነት ወይም የጎሣ ጦርነት አይደለም። ልክ በሌላ ሀገር እንደሚታየው በሀይማኖት ስም ጦርነት ትጀምራለህ። ቆየት ብለህ ወዴት አቅጣጫ እንደሚያመራ ታውቀዋለህ። ስለዚህ፣ አሉ የሚባሉት ዋነኞቹ ችግሮች ሁሉ ለውይይት ቀርበው በስፋት እና በአጠቃላይ ሊመከርባቸው ይገባል ብየ አስባለሁ። ይህ ካልሆነ ምንም ተስፋ አይኖርም። »
ጋዜጠኛው ኒህያል ቦል አሁን በደቡብ ሱዳን የሚታየውን ውዝግብ ለማብቃት እና ሀገሪቱን በተወሰነ ደረጃ ለማረጋጋት ቢያንስ አምስት ዓመት እንደሚያስፈልግ ይገምታል። ተፋላሚዎቹ ወገኖች በጠቅላላ ግን በወቅቱ ወሳኝ የሆነው ሀገሪቱን የማረጋጋት ፍላጎት ይኑራቸው አይኑራቸው አጠያያቂ መሆኑን ቦል ገልጸዋል።
ይህም በርስበርሱ ጦርነት ሰበብ የተፈናቀለውን ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጋውን ሕዝብ የምግብ እጥረት ችግር እና ስቃይ ይበልጡን እንደሚያባብሰው የርዳታ ድርጅቶች በማስጠንቀቅ፣ ሁኔታው ካለተቀየረ ሕዝቡ የረሀብ ደጋ እንደሚያሰጋው ገልጸዋል። ብዙዎችም ወደ ጎረቤት ዩጋንዳ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ተሰደዋል። ደቡብ ሱዳንን ሰሞኑን የጎበኙት የተመድ የአስቸኳይ ርዳታ አስተባባሪ መስሪያ ቤት፣ በምሕፃሩ የኦቻ ኃላፊ ጆን ጊንግ እንዳስታወቁት፣ አምስት ሚልዮን ደቡብ ሱዳናውያን በአሁኑ ጊዜ በምግብ ርዳታ ላይ ጥገኛ ናቸው። ያም ቢሆን አስቸኳዩ የሰብዓዊ ርዳታ አስፈላጊ መሆኑን ያሰማው ተማፅኖ ንዑሱን ትኩረት እና ምላሽ ብቻ ያገኘበትን ሁኔታ ጆን ጊንግ በጥብቅ ነቅፈዋል። ለደቡብ ሱዳን እንዲቀርብ ከተጠየቀው 1,3 ቢልዮን ዶላር ርዳታ መካከል እስካሁን የተሸፈነው 24 ከመቶው ብቻ ነው። የኦቻ ኃላፊ ጆን ጊንግ አክለውም ተፋላሚዎች ወገኖችም ለርዳታ ድርጅቶች ስራ አክብሮት ሳይሰጡ ርዳታ የጫኑ ካሚዮኖችን አጥቅተዋል፣ የርዳታ ቁሳቁስ ማከማቺያ መጋዘኖችን ዘርፈዋል በሚል ጠንካራ ወቀሳ ሰንዝረዋል።
አርያም ተክሌ
አዜብ ታደሰPost Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”