በውጭ አገር አብራሪዎች ላይ የተማመነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

በውጭ አገር አብራሪዎች ላይ የተማመነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ

Unread post by zeru » 08 Mar 2014 19:21

Image

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዛሬ 68 ዓመታት በፊት ሥራ የጀመረው አሜሪካውያን አውሮፕላን አብራሪዎችን በመያዝ ነበር፡፡ ከአስራ አንድ ዓመታት በኋላ በ1949 ዓ.ም የአቪየሽን አካዳሚ ከፍቶ የራሱን አብራሪዎችና የበረራ አስተናጋጆች እንዲሁም ቴክኒሻኖችን ማሰልጠን ጀመረ፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪዬሽን አካዳሚ በአብራሪነት ለመሰልጠን የሚፈልጉ አመልካቾች በጠቅላላ እውቀት፣ በቋንቋ፣ በሂሳብና በፊዚክስ የትምህርት ዘርፎች ላይ ያተኮረ የመግቢያ ፈተና ይወስዱ ነበር። ቀጣዩ የቃል ፈተና ሲሆን ከዚያም የጤና ምርመራ ማድረግ ይከተላል፡፡ አመልካቾች እነዚህን ሁሉ በብቃት ካለፉ በኋላ ነው የአቪዬሽን አካዳሚው የበረራ ሰልጣኝ የሚሆኑት፡፡ አካዳሚው በተከፈተ የመጀመርያዎቹ ዓመታት በአብራሪነት ለመሰልጠን እስከ 1ሺ የሚደርሱ አመልካቾች ይመዘገቡ የነበረ ቢሆንም ተቀባይነት አግኝተው የሚሰለጥኑት ግን ከ20 አይበልጡም ነበር፡፡
በአቪዬሽን አካዳሚው አንድ አብራሪን አሰልጥኖ ለማውጣት ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ የጠቆሙት ምንጮች፤ አብራሪው ይህንን ወጪ ለመሸፈን ተመርቆ ከወጣ በኋላ አየር መንገዱን ለ9 ዓመት የማገልገል ግዴታ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ በቀድሞው የአቪዬሽን አካዳሚው አሰራር፤ የአብራሪነት ሙሉ ስልጠናን ለማጠናቀቅ 2 ዓመት የሚፈጅ ሲሆን በዚሁ ጊዜ ውስጥ ሰልጣኙ ከአካዳሚክ ትምህርት ባሻገር፣ እስከ 200 ሰዓት የተግባር የበረራ ስልጠና ይሰጠዋል፡፡ ተጨማሪ የ50 ሰዓት በረራም በ‹‹ሲሙሌተር›› ይማራል። ሲሙሌተር፤ከመሬት የማይነሳ፣ በአየር ላይ የማይበር፣ ኮምፒውተራይዝድ የሆነና የአውሮፕላን በረራን ለመለማመድ የሚያስችል የማሰልጠኛ ማሽን ነው፡፡ አካዳሚው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሰራሩን የቀየረ ሲሆን የአብራሪነት ሥልጠናው እንደቀድሞው ሁለት ዓመት ሳይሆን በ1 ዓመት ከ2 ወር ይጠናቀቃል፡፡
አብራሪዎች ስልጠናውን እንዳጠናቀቁ በቀጥታ ወደ አውሮፕላን በረራ አይገቡም፡፡ ልምድ ያላቸው አብራሪዎች በሚያበሩበት አውሮፕላን ውስጥ ሶስተኛ ሰው ሆነው “ታዛቢ” ወንበር ላይ በመቀመጥ ልምድ ይቀስማሉ፡፡ ሂደቱ በዚህ ብቻ ግን አያበቃም፡፡ በሲሙሌተር ላይ የማብረር ችሎታቸውን ይፈተናሉ። ይህን ፈተና ያለፉ እጩዎች፣ ረዳት አብራሪ በመሆን ከዋናው አብራሪ ጋር መስራት ይጀምራሉ፡፡ ይሄም እስከ አምስት ወራት ድረስ ሊፈጅባቸው ይችላል፡፡
ከትንሽ አውሮፕላን ወደ ትልቅ ለመሸጋገር ሥልጠናና ፈተና ይኖራል፡፡ የአብራሪነት ፈቃድ ለማደስም ሁሉም አብራሪዎች ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡ ይሄ ሁሉ የሚሆነው በሲሙሌተር ሲሆን ሲሙሌተሩ ደግሞ “አንድ ለእናቱ” ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከዓመት ዓመት በሥራ እንደተጠመደ ይዘልቃል፡፡ ከውጭ አገር የሚመጡ ዋና አብራሪዎች ከማንኛውም የበረራ ምደባ በፊት ፈተና የሚወስዱት በዚሁ ሲሙሌተር ሲሆን ምሩቅ አብራሪዎች ይህን ወረፋ በትእግስት ጠብቀው ልምምዳቸውን ማድረግ ግድ ይሆንባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ሰዓት በሚከተለው መመሪያ መሰረት፤ የበረራ ፈቃድ ለማደስ ዋና አብራሪ በየ 6 ወሩ፤ ረዳት አብራሪ ደግሞ በየዓመቱ የበረራ ብቃታቸውን በሲሙሌተሩ እየተፈተኑ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል። በዋና አብራሪውና በረዳቱ መካከል ያለው ዋና ልዩነት የበረራ ልምድ ሲሆን ልምዱ የሚለካውም በበረራ ሰዓት ብዛት ነው፡፡ ቦይንግ 737 ለማብረር የሚመደቡ ዋና አብራሪዎች፤ እስከ 13ሺ ሰዓታት ያበረሩ እንዲሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን በዚህ አውሮፕላን ውስጥ ከረዳት አብራሪነት ወደ ዋና አብራሪነት ለመሸጋገር ከፈጠነ እስከ 8 ዓመት፣ ከዘገየ ደግሞ 10 ዓመት ይወስዳል፡፡
ረዳት አብራሪ ወደ ዋና አብራሪነት የሚሸጋገርበት ሂደት ግልፅ አይደለም የሚሉ ረዳት አብራሪዎች፤ ወደ ዋና አብራሪነት ደረጃ የሚያድጉት በአንጋፋ ዋና አብራሪዎች ግምገማ እንደሆነ ጠቅሰው ብዙ ጊዜ ዋና አብራሪዎች ብቃታቸውን የሚፈትኑት በግል ባህርያቸው ላይ ተመስርተው ነው ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡
አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ረዳት አብራሪዎች አብረዋቸው የሚሰሩት ዋና አብራሪዎች የውጭ ዜጐች ቢሆኑ ይመርጣሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የሚበዙት ኢትዮጵያዊያን ዋና አብራሪዎች በረዳት አብራሪዎቹ ላይ ጫና እና ጭቅጭቅ ስለሚያበዙ እንደሆነ ያነጋገርናቸው የበረራ ባለሙያዎች ገልፀዋል፡፡ ብዙዎቹ ዋና አብራሪዎች እስከ 60 ዓመት ዕድሜያቸው የሚበሩ ሲሆን እንዳላቸው ልምድና የማብረር ብቃት ከጡረታ በኋላ ለተጨማሪ 5 ዓመታት በማብረር እስከ 65 ዓመታቸው ድረስ አየር መንገዱን ያገለግላሉ፡፡
አየር መንገዱ ባለፉት 5 ዓመታት በርካታ አውሮፕላኖችን የገዛ ሲሆን የበረራ መዳረሻዎቹ መጨመራቸውም ይታወቃል፡፡ ይሄን ተከትሎም የውጭ አገር ዋና አብራሪዎች በብዛት ተቀጥረዋል። 75 በመቶ ያህሉ የአየር መንገዱ አብራሪዎች የውጭ ዜጎች እንደሆኑ የድርጅቱ መረጃ ይጠቁማል። እነዚህ አብራሪዎች በበረራ ሰዓት ልምዳቸው ከኢትዮጵያውያኑ በእጥፍ የሚልቁ ናቸው፡፡
አብራሪዎቹ የሚከፈላቸው ደመወዝ በአለም አቀፍ የደመወዝ መስፈርት መሰረት በመሆኑ ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡ በዚያ ላይ የውጭዎቹ አብራሪዎች ያለእረፍት ለበርካታ ሰዓታት ስለሚያበሩ ዳጐስ ያለ ክፍያ ያገኛሉ፡፡ ሆኖም አብራሪዎቹ ከሁለትና ሶስት ዓመታት በላይ በአየር መንገዱ አይቆዩም፡፡ ያለ እረፍት በመስራት የሚያገኙት ክፍያ ጠቀም ያለ ስለሆነ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የሰሩበትን ይዘው ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ምንጮቻችን ገልፀውልናል፡፡ በዚህም የተነሳ አየር መንገዱ በየጊዜው አዳዲስ የውጭ አብራሪዎችን ለመቅጠር ይገደዳል። በዚያ ላይ ኢትዮጵያዊያኑ አብራሪዎችም አየር መንገዱን እየለቀቁ በሌሎች አገራት አየር መንገዶች እንደሚቀጠሩ ምንጮች ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን አብራሪዎች በደሞዝ ማነስ፣ ከውጪ አገር አብራሪዎች ጋር እኩል ባለመታየት እንዲሁም በየሰበቡ በሚጣልባቸው ቅጣትና የስራ ደህንነት ማጣታት በእጅጉ እንደተማረሩ ይገልፃሉ፡፡ ማናቸውም አብራሪዎች የሚከፈላቸው ደሞዝ እንደበረራ ሰዓታቸው፣ እንደሚያበሩት አውሮፕላንና እንደየሚሄዱበት አገር ምንዛሪ የሚለያይ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያኖቹ አብራሪዎች በረዳት አብራሪነት ስራ ሲጀምሩ 7ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ የሚከፈላቸው ሲሆን የበረራ ሰዓታቸው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ክፍያቸውም እንደሚያድግ ምንጮች ይገልፃሉ፡፡ እንደ ቦይንግ 737 እና 767 ያሉ አውሮፕላን አብራሪዎች ደግሞ እስከ 30 ሺህ ብር የወር ደመወዝ ይከፈላቸዋል፡፡
አየር መንገዱ የአቪዬሽን አካዳሚውን ከከፈተ ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 57 ዓመታት ያሰለጠናቸው ኢትዮጵያውያን አብራሪዎች ብዛት 975 ሲሆኑ 3079 ቴክኒሺያኖችንና ከ4 ሺህ በላይ የበረራ አስተናጋጆችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ማሰማራቱን ከአየር መንገዱ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት አየር መንገዱ 800 ያህል አብራሪዎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቀጠሩ የወጭ አገር ዜጎች መሆናቸውንም እነዚህ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በ51 አገራት 87 መዳረሻዎች ያሉትና 144 በረራዎችን በየቀኑ በማድረግ በዓመት 4.5 ሚሊዮን ተጓዦችን የሚያስተናግደው አየር መንገዱ፤ ከቅርብ አመታት ወዲህ እያሰለጠነ ወደ ስራ የሚያሰማራቸው የበረራ አስተናጋጆች ቁጥር እየጨመረ ቢሄድም በአየር መንገዱ ውስጥ በስራ ላይ ያሉ የበረራ አስተናጋጆች ቁጥር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መምጣቱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ለበረራ አስተናጋጅነት ሰልጥነው ከሚቀጠሩት መካከል ቀላል የማይባሉት በደሞዝ ማነስ፣ የስራ እድገት ባለማግኘት፣በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች አለመሟላትና በሰራተኛ አያያዝ ችግር ሳቢያ ስራቸውን ለመልቀቅ ይገደዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ አንዲት በበረራ አስተናጋጅነት ተቀጥራ የምትሰራ ሆስተስ፤ ያለባትን የአየር መንገዱን እዳ ሳትከፍል መልቀቅም ሆነ ወደ ሌሎች አየር መንገዶች መዛወር አትችልም፡፡ በዚህም የተነሳ ለስራ በየሄዱባቸው አገራት የሚቀሩ እንዳሉ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ነግረውናል፡፡
አየር መንገዱ ለበረራ አስተናጋጅነት ስልጠና በሚሰጥበት ወቅት ከንድፈ ሃሳብና ከተግባር ትምህርቱ በተጨማሪ የስራ ላይ ስልጠና (on job training) ሲሰጥ የኪስ ገንዘብ ስለሚከፈል አንዲት የበረራ አስተናጋጅ ሰልጣኝ የ300ሺህ ብር ባለዕዳ ሆና ነው የምትመረቀው፡፡ ለዚህም ነው እስከ 6 ዓመት ድረስ የማገልገል ግዴታ ያለባት። ማንኛዋም የበረራ አስተናጋጅ ስልጠናዋን ጨርሳ ከተመረቀችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 5 ዓመት ድረስ ነፃ የአውሮፕላን ትኬት አይፈቀድላትም፡፡ ይህም የሚደረገው ዕዳዋን ሳትከፍል ወደ ውጪ አገር እንዳትሄድ ታስቦ ነው ይላሉ-ምንጮች፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በበረራ አስተናጋጅነት ተቀጥረው የሚሰሩ የተለያዩ አገራት (በተለይም ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ አገራት ዜጎች) አሉ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ቻይናውያን በበረራ አስተናጋጅነት ተቀጥረው የነበረ ቢሆንም ዓመት ያህል እንኳን ሳይሰሩ ለቀው እንደሄዱ ታውቋል፡፡
በበረራ አስተናጋጅነት ሙያ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ የቆዩት ሆስተሶች (ሲኒየር ሆስተሶች) የተሻለ ደመወዝና ጥቅማጥቅም ቢከፈላቸውም አብዛኞቹ በስራቸው ደስተኞች እንዳልሆኑ ይነገራል፡፡ አየር መንገዱ ከአምስት ዓመት በፊት ለጀማሪ ሆስተስ ይከፍል የነበረውን 1200 ብር ወርሃዊ ደሞዝ አሁን ወደ 2500 ብር ቢያሳድግም አስተናጋጆቹ በበዛ የሥራ ጫና፣ በሥራ ደህንነት ማጣትና በየሰበቡ በሚጣልባቸው ቅጣት መማረራቸውን ይገልፃሉ። የስድስት ዓመት አገልግሎታቸውን የጨረሱ አስተናጋጆችን የኢምሬትስ እና የሳውዲ አየር መንገዶች እስከ 1 ሺ ዶላር (20ሺ ብር ገደማ) ወርሃዊ ደሞዝ በመክፈል እየቀጠሯቸው እንደሆነ ለማወቅ ችለናል፡፡ ሆስተሶቹ ከሰራተኛ አያያዝ ጋር በተገናኘ የሚገጥሟቸውን ችግሮችና ጠንከር ያሉ የመብት ጥያቄዎችን ካነሱ የደመወዝ፣ የጥቅማጥቅም ቅጣቶችና የዲሲፕሊን እርምጃዎች እንደሚወሰድባቸው ይገልጻሉ፡፡ የስራ ደህንነት ማጣትም ዋንኛው ችግራችን ነው ይላሉ፡፡
ስድስት ሺህ ቋሚ ሰራተኞች እና አንድ ሺህ ጊዜያዊ ሰራተኞ እንዳሉት የሚነገረው አየር መንገዱ፤ ከሰራተኞቹ ውስጥ 600 የሚሆኑት በአለም አቀፍ ደመወዝ መስፈርት ክፍያ የሚፈፀምላቸው የውጭ አገር ዜጎች ናቸው፡፡ አየር መንገዱ እ.ኤ.አ ከ2009-2011 ዓ.ም ድረስ ከፍተኛ ትርፍ ያገኘ ሲሆን ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ አትርፏል፡፡ ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም ትርፉ ወደ 734 ሚሊዮን ብር ወርዶ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት 62 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን 33 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ውል ፈፅሟል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ 787 ድሪም ላይነር ሲሆኑ አስራ አራቱ ደግሞ ኤርባሶች ናቸው፡፡
የሰራተኞቹን በተለይም የአውሮፕላን አብራሪዎችና የበረራ አስተናጋጆቹን ቅሬታና ወደ ተለያዩ አገራት የሚፈልሱ ባለሙያዎችን በተመለከተ የአየር መንገዱን ሃላፊዎችን አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡
addis admas

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”