የቀድሞ የህወሓት ታጋዮች ቅሬታቸው ገለፁ (ከአብርሃ ደስታ)

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

የቀድሞ የህወሓት ታጋዮች ቅሬታቸው ገለፁ (ከአብርሃ ደስታ)

Unread post by zeru » 04 Mar 2014 19:08

ባሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የዉኃና አፈር ጥበቃ (Water and Soil Conservation, ማይን ሓመድን ዕቀባ) ተግባራት የሚከናወኑበት ግዜ ነው። ህዝብ ስራው ትቶ ተገዶ በፕሮግራሙ ይሳተፋል። ለፖለቲካ ሲባል ህዝብ በፍላጎቱ ተሳተፈ ተብሎ ሪፖርት ይቀርባል። እውነታው ግን ሌላ ነው። በየዓመቱ ህዝብ ሳያምንበት ተገዶ ይሰራል። በግዜው ያልሰራ እስከ ሦስት መቶ (300) ብር ተቀጥቶ ይሰራል። በዚሁ ምክንያት ብዙ ሌሎች የግል ሥራዎች ይቆማሉ። ዜጎች ብዙ ኪሳራ ይደርስባቸዋል።
የዉኃና አፈር ጥበቃ ሥራ የጉልበት ስራ ነው። መስራት የሚችል ይሰራል፣ ወይ እንዲሰራ ይገደዳል። በአፅቢ ወንበርታ ወረዳ ጣብያ ሩባ ፈለግ ግን ለየት ያለ ጉዳይ ተከስቷል። የዓፅቢ ወንበርታ ህዝብ በህወሓት የትጥቅ ትግል ወቅት ንቁ ተሳታፊ የመኖሩ ያህል ባከባቢው ብዙ አካል ጉዳተኞች (የቀድሞ ታጋዮች) አሉ። በጉልበት ስራ መሰማራት አይችሉም። ምክንያቱም አካላቸው ጎድሏል። እናም በጡረታ ገንዘብ በገጠር ህይወት ነው የሚኖሩ። የአካል ጉዳተኞች መሆናቸው ታውቆ ላለፉት ሃያ ሦስት (23) ዓመታት በዉሃና አፈር ጥበቃ ሥራ ተሳትፈው አያውቁም። ምክንያቱም አካላዊ ቁመናቸው አይፈቅድላቸውም፤ ግማሾቹ ዓይናቸው የጠፋ ግማሾቹ እግራቸው የተቆረጠ ወዘተ ናቸው።
አሁን ግን ለመጀመርያ ግዜ በተለየ ሁኔታ አካላቸው የጎደሉ የቀድሞ የህወሓት ታጋዮች በዉኃና አፈር ጥበቃ ፕሮግራሙ እንዲሳተፉ በመንግስት አካላት እየተገደዱ ይገኛሉ። ለምን አሁን እነሱን ማስገደድ ተጀመረ? የአፅቢ ወንበርታ ህዝብ በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት በመንግስት አካላት ላይ ተቃውሞ አስነስቶ ነበረ። ህወሓቶች የቀድሞ ታጋዮቹ ዒላማ አድርገው በዉኃና አፈር ጥበቃ እንዲሳተፉ ያስገደዱበት ምክንያትም ህዝብ ፀረመንግስት ሲነሳ የቀድሞ ታጋዮቹ ከመንግስት ጎን ከመሰለፍ ይልቅ የህዝቡን ጥያቄ በመደገፋቸው ነው። ታጋዮቹ ዓፈና በዝቷል፤ ለዚህ አይደለም መስዋእት የከፈልነው፣ ፍትሕ ጠፍቷል ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች በማንሳታቸው ነው።
አሁን የድሮ ታጋዮቹ በግዝያቸው በፕሮግራሙ ባለመሳተፋቸው የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸው ለብቻቸው እንዲሳተፉ ይደረጋል። የገንዘብ ቅጣቱ እስከ ሦስት መቶ ብር ይደርሳል። ሦስት መቶ ብር ደግሞ መክፈል አይችሉም፤ ግድቡም መገደብ አይችሉም። ምክንያቱም ታጋዮቹ የሚተዳደሩት በጥሮታ ገንዘብ ነው። የጥሮታ ገንዘቡ ደግሞ ከሦስት መቶ ብር በላይ አይደለም። ታድያ ሦስት መቶ ብር (የጥሮታ) ለመንግስት ከፍለው በምን ሊተዳደሩ? ምን በልተው ሊገድቡ? በግድቡ ለመሳተፍም ይከብዳቸዋል። ምክንያቱም ግድብ የጉልበት ስራ ስለሆነ። አካላቸው አይፈቅድላቸውም፤ ምክንያቱም አካል ጉዳተኞች ናቸው።
በዚሁ ምክንያት በአፅቢ ወንበርታ ወረዳ ሩባፈለግ ጣብያ ከባድ ዉጥረት ነግሷል። በጣብያው (ንኡስ ወረዳ) እስካሁን ድረስ 963 ዜጎች በፕሮግራሙ ባለመሳተፋቸው ምክንያት ክስ ተመስርቶባቸዋል። ክስ ከተመሰረተባቸው ዜጎች ከ100-150 የሚደርሱ ሰዎች ተቀጥተዋል። ሌሎችም ቅጣታቸው እየተጠባበቁ ነው። የአከባቢው ህዝብ የካቲት 13, 2006 ዓም ይህ የመንግስት ካድሬዎች ተግባር በመቃወም “ሰሚ የለም ወይ?!” በማለት በጭኾት ተቃውሞውን አሰምቶ ነበረ።

የቀድሞ ታጋዮቹ ግን መንግስትን ክፉኛ እየወቀሱ ነው። አካላቸው በመጉደሉ ምክንያት ምንም ዓይነት የጉልበት ስራ መስራት የማይችሉ የመንግስት ተግባር ስለተቃወሙ ብቻ አሁን በፕሮግራሙ እንዲሳተፉ እየተገደዱ ካሉ የቀድሞ የህወሓት ታጋዮች መካከል ስማቸው እንዲጠቀስ ፍቃደኛ ከሆኑ (1) ሃምሳአለቃ ሃይለማርያም ገብረእግዚኣብሄር፣ (2) ሃምሳአለቃ አታኽልቲ ገብረኪሮስና (3) አስራአለቃ ወልዴብርሃ ገብረመድህን ይገኙባቸዋል። እነዚህ ሰዎች ደርግ ከወደቀ ከ1983 ዓም ጀምሮ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት በምንም ዓይነት የመንግስት የጉልበት ስራ ተሳትፈው አያውቁም። አሁን መቃወም በመጀመራቸው ግን እየተገደዱ ይገኛሉ። አሁንም ቢሆን በጉልበት ሊገድቡ እንደማይችሉ የታወቀ ነው። የመንግስት ጥረት ግን ታጋዮቹ መንግስትን መቃወም እንደማያዋጣቸው ተገንዝበው ተቃውሞአቸውን እንዲያቆሙ ለማስገደድ ብቻ ነው። መንግስትን ከደገፉ ግን ነፃ ይሆናሉ። አይገደዱም። እንዲህ ነው የህወሓት ተቃውሞን የማፈን ስትራተጂ።
ቀደም ሲል የህወሓት ካድሬነታቸው በማቆማቸው ምክንያት መሳርያቸውን (ጠመንጃቸውን) በመንግስት አካላት ተነጥቀዋል። በአካላዊ ጉዳት ምክንያት ከህወሓት ዉትድርና ቢወጡም ጠመንጃቸው ግን ይዘውት ነበር የሚኖሩ። ጠመንጃቸው ይፈልጉታል። ምክንያቱም (አንድ) ራሳቸው የሚከላከሉበት ነው። ለብዙ ዓምታት ከነሱ ጋር የኖረ ስለሆነ ማንነታቸው አድርገውታል። እናም ጠመንጃቸውን ሲነጠቁ insecurity ይሰማቸዋል። ትልቅ የሞራል ውድቀት ይሰማቸዋል። የሞራል ኪሳራ ይደርስባቸዋል። ህወሓትም ይህን ያውቃል። እናም ነጠቃቸው። (ሁለት) ጠመንጃቸው በትንንሽ ከተሞች የሚገኙ ሃብታም የህወሓት ካድሬዎች የቤት ዘበኞች በመሆን ስራ የሚያገኙበት ነው። ጠመንጃ ከሌላቸው በዘበኝነት የመቀጠር ዕድል አያገኙም። ስለዚህ ስራ እንዳያገኙ ስለተፈለገ ነው። ስራ ካላገኙ በመንግስት ጥገኛ ይሆናሉ። ጥገኛ ከሆኑ ደግሞ መንግስትን ይደግፋሉ እንጂ አይቃወሙም። መንግስትን ካልተቃወሙ ደግሞ ህወሓት የፈለገውን ዓፈና የማድረስ መብት አገኘ ማለት ነው። ስለዚህ የዚህ ሁሉ ዓላማ ተቃውሞውን በማዳከም ህዝብን መጨቆን የሚቻልበት መንገድ ማመቻቸት ነው።
በብዙ የትግራይ አከባቢዎች የዉኃና አፈር ጥበቃ ፕሮግራም እየተሰራበት ያለ ሲሆን ባከባቢው ተገኝቶ በፕሮግራሙ ያልተሳተፈ ገበሬ መሬቱ እየተነጠቀ ይገኛል (እንደ ቅጣት መሆኑ ነው)። ነገሩ እንዲህ ነው። የህወሓት ካድሬዎች ማዳበርያ ለመሸጥ ሲባል ገበሬውን በአስገዳጅ እንዲገዛ ያደርጋሉ። ማዳበርያ ካልገዛ ይታሰራል፣ የመንግስት አገልግሎት አያገኝም፣ መሬቱም ይነጠቃል። ገብሬውም እነዚህ ሁሉ ቅጣቶች መሸከም ስለማይችል የማዳበርያ ዕዳ ይገባል። ማዳበርያውን ለመግዛት ገንዘብ ከተለያየ ተቋማት ይበደራል። ብድሩ ለመመለስ በከተሞች አከባቢ ወይ ሌላ ራቅ ያለ ቦታ በመሄድ ተጨማሪ ስራ ይፈልጋል። ዕዳውን ለመክፈል ስራ ፍለጋ ከቀዩ ይርቃል። ካድሬዎች ደግሞ “ባከባቢው እያለማ አይደለም” በሚል ምክንያት መሬቱ ተወስዶ ለሌላ ካድሬ ይሰጣል። ገበሬው ለዘላለሙ ከቀዩ ይፈናቀላል። ምክንያቱም መሬት የመንግስት ነው። መሬት የኔ ነው ብሎ ፍርድቤት ሂዶ መከራከር አይችልም። ሁሉም ነገር በሕግ ሳይሆን በመመርያ ነው የሚሰራው። እናም ህዝብ ችግር ላይ ወድቋል።
የታጋዮቹ ጉዳይ ግን አሳሳቢ ነው። ታጋዮቹ አካላቸው ጎድሏል። እኛን ከጨቋኞች ነፃ ለማስወጣት ሲሉ መስዋእት ከፈሉ። ለኛ ሲሉ አካላቸው ጎደለ። አሁን መስራት አይችሉም። መቃወምም እንዳይችሉ እየተደረጉ ነው። እነሱ የቤት ስራቸው ጨርሰዋል። ለኛ ሲሉ አካላቸው የጎደሉ ወገኖች አሁን እኛ ልንተባበራቸው ይገባል። እኛ ልንታገልላቸው ይገባል። እኛ ነፃ ልናወጣቸው ይገባል። ምክንያቱም እነሱ ዓቅሙ የላቸውም፤ እንደ ድሮ ሩጠው ጫካ መግባት አይችሉም። ከዚሁ ዓፋኝ ስርዓት እንገላግላቸው።

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”