ኢትዮጵያዊነት – ”የለህም ይሉኛል፤ እውነት የለሁም ወይ?

ፖለቲካ ፣ ወቅታዊ ጉዳዮች
Politics , Current affairs
User avatar
zeru
Leader
Leader
Posts: 952
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

ኢትዮጵያዊነት – ”የለህም ይሉኛል፤ እውነት የለሁም ወይ?

Unread post by zeru » 08 Feb 2014 21:21

ከማንነት ጋራ የተያያዙ ጥያቄዎች፣ ሙግቶች፣ በተቃራኒውም አስቀያሚ ሐሳብ አልባ ስድድቦች ሰሞኑን በርከትከት ብለዋል። ጥያቄዎቹና ሙግቶቹ መኖራቸውን አጥብቄ እደግፈዋለሁ። በእኔ እይታ አብዛኞቹ ምልልሶች ወይም ሙግቶች በመሠረቱ አዲስ ጭብጥም ሆነ መከራከሪያ አላቀረቡም። ቢሆንም የነበረውንም ቢሆን በአግባቡ በተደጋጋሚ እያነሱ ሐሳብ መለዋወጡ ጠቃሚ ነው፤ ሙከራው ቢያንስ እርስ በርስ መተዋወቅን ይጨምራል፤ አልፎም አዲስ ሐሳቦችን ለማፍለቅ እድል ይሰጣል።
የማነ ናግሽ ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም፤ ያለው በብሔረሰብ ላይ የተመሰረተ ማንነት ብቻ ነው የሚለውን ሐሳብ በትግሪኛ ጽፎት ተመልክቼ ነበር። ኃላም ራሱ ወደ አማርኛ እንደመለሰው ይህን ጽሑፍ ወደማጠናቀቁ ስቃረብ ተመልክቻለሁ። በመሠረቱ ሐሳቡ አዲስ አይደለም። በየማነ አስተያየት መነሻነት ሌሎችም አመለካከታቸውን አካፍለዋል፤ ጥቂቶቹን በሚገባ አንብቤያለሁ። በሒደቱ የታየው ጉዳዩን ከመመርመር ይልቅ ተናጋሪውን የማጥቃት ስልት ጠቃሚ ስላልሆነ ወደዚያ አንመለሰም። በሐሳቡ ላይ ግን አስተያየቴን ላካፍል።
1. ስለማንነት እንደመነሻ
ሁልጊዜም ከጥንቱና ከስሩ መጀመር ጠቃሚ ቢሆንም ጽሑፌን ወደ መጽሐፍ ምእራፍነት እንዳይቀይረው በመስጋት፣ ከዚያ በላይ ደግሞ አንባቢዎቼ ስለማንነት እና ስለፖለቲካው መሠረታዊ ጉዳዮች ያውቃሉ ከሚል እምነት ስለማንነት ወደመዘርዘር አልገባም። በምትኩ ለክርክሬ የሚሆኑኝን መነሻዎች ብቻ እጠቅሳለሁ። አምስት ጭብጦች ላስይዝ፤
1.1. አንድ ሰው ብዙ አይነት ማንነቶች ሊኖሩት ይችላሉ፤ ይኖሩታልም። አንድ ማንነት በጉልህ የሚታየው ከሌላው ጋራ ሲነጻጸር እንደመሆኑ መጠን፣ አንድ ሰው ማንነቱን የሚገልጽበት መንገድ እንደሁኔታው ይለያያል። ጥያቄው ሃይማኖትን ሲከተል፣ ሃይማኖታዊ ማንነቱን ያስቀድማል እንደማለት። እዚህ የምናነሰው ግን ቋንቋን ጨምሮ ከተመሳሳይ ባህል፣ ታሪክ እና ስነልቦና ጋራ ስለተቆራኘው ማንነት ነው። የማንነት ፖለቲካ በአገራችን በዋናነት የሚወከለውም በዚሁ ነው። ለውይይታችን እንዲረዳ በብሔረሰባዊ እና በአገራዊ ማንነት ላይ ብቻ እናተኩር።
1.2.ማንነት (ብሔረሰባዊም ይሁን አገራዊ) ማኅበረሰብ ሠራሽ ነው፤ ተፈጥሯዊ አይደለም። ማንነት ከቤተሰብ፣ ከማኅበረሰብና ከትምህርት ቤት የምንማረው ነው። ስለዚህም ባለበት አይረጋም፤ መጠነኑና ፍጥነቱ ቢለያየም ይለወጣል።
1.3.ማንነት በአጋጣሚ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ በመወለድ እና/ወይም በማደግ፣ አለዚያም በተጽእኖ ሊገኝ ወይም ሊለወጥ ይችላል። ይህ ብቻ ግን አይደለም። ማንነት በምርጫም ሊገኝ ይችላል፤ አንድ ሰው በፍላጎቱ የአንድ ማንነት አካል ሊሆን ይችላል፤ ምን ያህል ይሳካለታል የሚለውን የሚወስኑ ብዙ ከእርሱ ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች ቢኖሩም። አንዳንድ ማኅበረሰቦችና ማንነቶች ከሌላው የበለጠ አዲስ መጤን የመቀበልና የማዋሐድ ጠባይ አላቸውና።
1.4. አንድ ማንነት ከቀላል ጀምሮ ወደ ውስብስብና ብዙ እንደሚያድግ ሁሉ፣ ማንነቶች ሊወራረሱ፣ አልፎም ማንነቶች ተደባልቀው/ተዋሕደው ”አዲስ/የተለየ” ማንነት ሊፈጥሩም ይችላሉ።
1.5. በማንኛውም መንገድ መስተጋብር የመፍጠር እድል ያገኙ ማንነቶች የተለያዩ እሴቶቻቸውን ይለዋወጣሉ፣ ይዋዋሳሉ፣ ያዳቅላሉ። እንዳለ የሚያስጠብቁት የማንነታቸው አካል መኖሩ እንደማይቀርም እሙን ነው። ስለዚህም ንጹህ የሚባል ማንነት አይኖርም። ንጹሕ የሚባል ማንነት ካለ ያ ማንነት በላቦራቶር የተፈጠረና እስካሁንም ወደምንኖርባት የሰው ዓለም ያልመጣ ማንነት
ከዚህ የሚከተለው ክርክሬ ቢያንስ በእነዚህ አምስት መንደርደሪያዎች ላይ የተመሠረተ ይሆናል። እነዚህን መነሻዎች ይዘን ወደ ጥያቄው እንመለስ። እውነት ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም?
በአገራችን የብሔረሰብ ማንነት አለ፤ ራሱን የዚህ ወይም የዚያኛው ብሔረሰብ አባል አድርጎ የሚመለከት ሰውም አለ። ይሄ ለክርክር የሚቀርብ፣ ያልተረጋገጠ ጉዳይ አይደለም። ይህኛው ቡድን ”ብሔርሰብ ነው ወይስ ዘውጌ ወይስ ጎሳ?” የሚለው ጥያቄ ላነሳነው ክርክር አስፈላጊ አይደለም። ለአሁኑ፣ ቁም ነገሩ፣ የራሳችን ባህላዊና ታሪካዊ ማንነት አለን የሚሉና ያላቸው ብድኖች መኖራቸው ነው። ስለዚህ ”እኔ የእገሌ ብሔረሰብ አባል ነኝ፤ የዚያኛው አይደለሁም፤ ማንነቴም አገው፣ ትግራዋይ፣ ጉሙዝ፣ ኦሮሞ፣ አማራ…ነው” የሚሉ ሰዎች አሉ። መኖራቸው እውነት ነው፤ በአግባቡ ከተያዘም ጸጋ ነው። አሁን የቀረበው ጥያቄ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት እነዚህ ብሔረሰባዊ ማንነቶች ብቻ ናቸውን የሚል ነው። ወይም፣ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለምን? እርግጥ የአንድ ማንነት ታጋሪዎች ነን የሚሉ ሰዎች እስካሉ ድረስ ስለማንነቱ ለማረጋገጥ ሌላ ምርመራ ማድረግ የግድ አይደለም ብሎ የሚከራከር ይኖር ይሆናል። በዚህ ስሌት፣ ”ኢትዮጵያዊ ማንነት አለን” የሚሉ ሰዎች መኖራቸው ብቻውን በቂ ማስረጃ በሆነ ነበር። ቢሆንም ተጨማሪ ሐሳቦችን መለዋወጡ አይጎዳም።
ለተጨማሪ ንባብ ይህን ይጫኑ

Post Reply

Return to “Ethio Politics .... ኢትዮ ፖለቲካ”