Page 1 of 1

የዛሬ ዓርብ ነሐሴ 4/2010 አበይት ዜናዎች - Wazema Radio

Posted: 10 Aug 2018 10:46
by selam sew
ለቸኮለ! የዛሬ ዓርብ ነሐሴ 4/2010 አበይት ዜናዎች

1. የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በም/ከንቲባ ታከለ ዑማ የቀረበለትን ካቢኔ አጽድቋል፡፡ ምክር ቤቱ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አካላት ማቋቋሚያ ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል፡፡ በታቦር ገብረመድሕን ምትክ አበበች ነጋሽ በአፈ ጉባዔነት ተመርጠዋል፡፡ ምክር ቤቱ ዛሬ ነሐሴ 4/2010 ሹመታቸውን ያጸደቀላቸዉ 18 የቢሮ ኃላፊዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
አልማዝ አብርሃ ሴቶችና ሕፃናት፣
ፍሬህይወት ተፈራ ፍትህ፣
ጀማሉ ጀምበር ወጣቶችና ስፖርት፣
ሺሰማ ገብረስላሴ ገቢዎች፣
ፍሬህይወት ገብረህይወት (ዶ/ር) የፐብሊክ ሰርቪስ፣
አሰፋ ዮሃንስ የቴክኒክና ሙያ፣
ኤርምያስ (ኢንጂነር) ኢንደስትሪ፣
አብዱልፈታ የሱፍ ንግድ፣
ፎኢኖ ፎላ ፋይናንስ፣
ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር) ኮንስትራክሽን፣
ሽመልስ እሸቱ (ኢንጂነር) መሬት ማኔጅመንት፣
ደረጀ ፈቃዱ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር፣
ዘውዱ ቀፀላ ሰራተኛና ማህበራዊ፣
ዮሃንስ ጫላ (ዶ/ር) ጤና፣
ሰናይት ዳምጠው (ኢንጂነር) ቤቶች አስተዳደር፣
ነብዩ ባየ ባህልና ቱሪዝም፣
ታቦር ገብረመድህን (ዶ/ር) ትምህርት፣
ንጋቱ ዳኛቸው የጥቃቅን እና አነስተኛ ቢሮ ኃላፊ ሆነዋል፡፡

2. የእንግሊዝ መንግስት የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይልን አሰልጥኗልና አስታጥቋል በሚል ሲወጡ የከረሙት ዘገባዎች የተሳሳቱ ናቸው ሲል አስተባበለ። በአዲስ አበባ የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ በላከልን መግለጫው እንግሊዝ በሶማሌ ክልል ከ 2013 እስከ 2015 ድረስ ድጋፍ ያደረገችው ህፃናትና ሴቶች ተኮር ለሆነ የፍትህ ስርዓት ማሻሻያ ነበር። ድጋፉ በ 2015 የፈረንጆች አቆጣጠር ማብቃቱን የኤምባሲው ቃል አቀባይ አስታውቀዋል።
ድጋፉ ሲደረግ የነበረው በእንግሊዝ አለማቀፍ ተራድኦ ድርጅት DFID በኩል ሲሆን በተደጋጋሚ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን እንግሊዝ ለሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ድጋፍ እንዳደረገች ተደርጎ መቅረቡ ስ ህተት መሆኑን አስገንዝቧል።

3. በዛሬው ዕለት በጂግጂጋ በተካሄደ ስብሰባ የሶማሌ ልዩ ኃይልና ሌሎች አካላት በመከላከያ ሠራዊቱ ዕዝ ሥር ሆነው እንዲሰሩ ተወሰነ። ኮማንድ ፖስትም ተቋቁሟል። የደቡብ ምስራቅ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል በላይ ስዩም፣ የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር እና ሌሎች የፀጥታ ሃይል አዛዦች በተገኙበት በጂግጂጋ ከተማ በተካሄደ ውይይት የፌደራልና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች በትብብር እና በቅንጅት ለመስራት ተስማምተዋል ተብሏል።

4. ኮንግረስማን ማይክ ኮፍማን ለጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ አድናቆት ቸረዋል፡፡ ዐብይ ከኤርትራ ጋር ሠላም በማውረዳቸውና እስረኞችን በመፍታታቸው ያሞገሱት ማይክ ኮፍማን ኢትዮጵያን የመጎብኘት ጉጉት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ሪፐብሊካኑ የኮሎራዶ ተወካይ ኮፍማን በኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት እንዲከበር የሚጠይቀውን ኤች.አር 128 የተሰኘ ረቂቅ በመደገፍ ይታወቃሉ፡፡ ማይክ ኮፍማን ለቪኦኤ በሰጡት ማብራሪያ “የቀድሞው የኢትዮጵያ መንግስት እንዳሁኑ ሁሉ በአሸባሪነት ላይ በሚደረገው ትግል ይተባበር ነበር፤ ዩናይትድ ስቴትስ ቅድሚያ የሰጠችው በአሸባሪነት ላይ ስለነበር ሠብዓዊነትን በሚመለከት ቸልተኝነት አሳይታለች፤ ይሕም ትልቅ ስሕተት ነበር፤ ዩናይትድ ስቴትስ እንደዚያ ያለ ስሕተት መድገም የለባትም” ብለዋል፡፡

5. የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዳይሬክተር ጃዋር መሐመድ ዛሬ በባሕር ዳር ብሉ ናይል ሆቴል ከክልሉ ወጣቶች ጋር ተወያያቷል፡፡ “ባለፉት ዓመታት አማራ እና ኦሮሚያን ለመከፋፈል እሳትና ጭድ ላቀበሉን፣ ሞተንም ቢሆን አሁን የምንፈልገው ኢትዮጵያዊነት ላይ ደርሰናል” ብሏል፡፡ “ለአማራ ብሔርተኝነት መጎልበት እኔም ከእናንተ ጋር አብሬ እሠራለሁ” ያለው ጃዋር የአዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነት ጉዳይን በተመለከተ ለቀረበ ጥያቄ ሲመልስ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ እና የአማራ ብቻ አይደለም፤ የጉራጌው፣ የሶማሌው… የሁሉም ሕዝቦች መሆኑን ማወቅ ይገባል” ነው ያለው፡፡

6. በተሰናባቹ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ኢሌ ከአንድ ወር በፊት ለእስር ተዳርገው የነበሩት የምክር ቤት አባል ከወሕኒ መውጣታቸው ተነገረ፡፡ የተከበሩ አብዲ አብዱላሂ (አብዲ ደሬ) ያለ መከሰስ መብታቸው ተነስቶ ለእስር የተዳረጉት በሶማሌ ክልል የሚፈጸመውን የመብት ጥሰት በማጋለጥ ለፓርላማ ደብዳቤ በመጻፋቸው ምክንያት ነበር፡፡

7. ኢትዮጵያ የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጠጠር ቅድመ ቁጥጥር ጀመረች፡፡ በአፋር 800 ሰዎች በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) መያዛቸውን ተከትሎ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባደረገው ክትትል ለወረርሽኙ መንስዔ የአዋሽ ወንዝ ውሀ ብክለት መሆኑን ደርሶበታል ተብሏል፡፡ በዲሞክራቲክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ ምልክት መታየቱን ተከትሎም በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የማቆያ ማዕከል እንዲሁም በቦሌ ጤና ጣቢያ የኢቦላ ሕክምና አሀድ አዋቅሯል፡፡

8. ኤመሬትስ ከአሰብ ወደብ ወደ አዲስ አበባ የነዳጅ ቱቦ ዝርጋታ ጥናት ለማካሄድ ከኢትዮጵያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት አደረገች፡፡ ይሕ የተገለጸው ዛሬ ጧት ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ከኤመሬትስ የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሪም አል ሀሺሚ ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡ የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ በአሰብ ወደብ የጦር ሠፈር በመገንባቷ በኢትዮጵያ የወደቡ አጠቃቀም ዙሪያ ጥያቄ ሲነሳ ሠንብቷል፡፡ ይሕ በእንዲህ እንዳለ የሳዑዲ ውጪ ጉዳይ ማኒስትር አዲል ቢን አሕመድ አል ጁቤር ትናንት በአስመራ ከፕ/ት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተው ከጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ጋር ተገናኝተዋል፡፡

9. የኤርትራ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልሕ ዛሬ አመሻሹ ላይ አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሚመሩት የኤርትራ ልዑክ ውስጥ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ የማነ ገብረአብ ይገኙበታል፡፡ የጉብኝቱ ዓላማ ሁለቱ ሀገራት በመሪዎች ዙሪያ በተፈራረሟቸው ጉዳዮች ዙሪያ ዝርዝር ንግግር ማድረግ ይሆናል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚገኙበት የቴክኒክ ኮሚቴ በድንበር፣ በንግድና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ ተጨማሪ ውይይት በማካሄድ ስምምነቶችን የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

Source: Wazema Radio Facebook Page