የዛሬ ዓርብ ሐምሌ 27/2010 አበይት ዜናዎች - Wazema Radio

Daily Ethiopian News, አዳዲስ ዜናዎች።
Forum rules
** When you post a News please include the Source link.
For More Ethiopian News please visit the Home Page
http://ethiopiaforums.com/
selam sew
Leader
Leader
Posts: 599
Joined: 08 Feb 2011 11:14
Contact:

የዛሬ ዓርብ ሐምሌ 27/2010 አበይት ዜናዎች - Wazema Radio

Unread post by selam sew » 03 Aug 2018 18:21

ለቸኮለ! የዛሬ ዓርብ ሐምሌ 27/2010 አበይት ዜናዎች

1. ድሬዳዋ ከተማ በጸጥታ ሥጋት ውስጥ በመውደቋ የጸጥታ ክትትል የሚያደርግ ኮማንድ ፖስት ተቋቋመ፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ የሚመራው ኮማንድ ፖስቱ መከላከያና ፌደራል ፖሊስን በማካተት ዘጠኙን ቀበሌዎች የሚቃኙ አራት ክፍሎች ይዞ ተመስርቷል፡፡ የከተማይቱ ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን “…በከተማዋ ሠላምና ጸጥታ ለማደፍረስ ድብቅ ዓላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ” ትዕዛዝ መተላለፉን ገልጸዋል፡፡ አንድ ብሔር ከሌላው ጋር እንደተጋጨ በማስመሰል፣ የውሸት መረጃ በመበተንና በማሕበራዊ ሚዲያ በማስተላለፍ ግጭት ለመቀስቀስ እየተሞከረ መሆኑን እንደደረሱበትም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ሳምንትም ወጣቶችን በማደራጀትና በተለያዩ ጥቅሞች በመደለል፣ አንዳንድ ባለንብረቶችም ተሸከርካሪያቸውን በመስጠት ሠላም ለማደፍረስ ሲሞክሩ መገኘታቸው ተጠቁሟል፡፡

2. የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ ታከለ ዑማ ዛሬ ጧት ከሁለቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርኮች ጋር መወያየታቸውን በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡ 4ኛው ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስና 6ኛው ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ዕርቀ ሠላም ወርዶ ዳግም በመገናኘታቸው መደሰታቸውን የገለጹት ከንቲባው የከተማ መስተዳድሩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከሁለት ወደ አንድነት የመጣው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ አባቶች በዛሬው ዝግ ጉባዔ የአንድነትና ትውውቅ ሥነ ሥርዓት አከናውነዋል፤ በነገው ዕለትም በሚሌኒየም አዳራሽ ሁለቱ ፓትሪያርኮች የሚገኙበት ፕርግራም ይካሄዳል፡፡

3. በመስቀል አደባባዩ የቦምብ ፍንዳታ ቀጥተኛ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ አምስት ተጠርጣሪዎች ከ15 ቀን በኋላ መደበኛ ክስ እንደሚከፈትባቸው ተጠቆመ፡፡ መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ ለዐቃቤ ሕግ መላኩን ዛሬ ለፍርድ ቤት አሳውቋል፡፡ ለሁለት ሰዎች ሕልፈትና ለ150ዎች ጉዳት ምክንያት በሆነው የቦምብ ፍንዳታ አቀነባባሪነትና ወንጀለኞችን ለማስመለጥ በመሞከር ነሐሴ 11/2010 መደበኛ ክስ የሚከፈትባቸው ተጠርጣሪዎች አብዲሳ ቀነኒ፣ ደሳለኝ ተስፋዬ፣ ጌቱ ግርማ፣ ሕይወት ገዳ እና ባሕሩ ቶላ ይባላሉ፡፡ በፍንዳታው ወቅት የአዕምሮ ሕመምተኛ መስላ ትንቀሳቀስ ነበር የተባለችው አራተኛ ተከሳሽ በአማኑኤል ሆስፒታል የምትገኝ ከመሆኑ በቀር የተቀሩት ተከሳሾች በዛሬው ዕለት ችሎት ተገኝተዋል፡፡

4. የአንድነት ፓርቲ አመራር የነበረው አንዷለም አራጌ የጻፈው “በዘመናት መካከል” የተሰኘ መጽሐፍ ከዛሬ ጀምሮ ለገበያ ውሏል፡፡ በጸረ ሽብር ሕጉ ተከሶ ለ6 ዓመት ተኩል ወሕኒ የቆየው አንዷለም ከወራት በፊት ከእስር መፈታቱ ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ የመጽሐፍ ምረቃ መረጃ… የኢሕአፓ መስራች በሆኑት ክፍሉ ታደሰ የተደረሰው “ኢትዮጵያ ሆይ” መጽሐፍ በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይመረቃል፡፡ “ኢትዮጵያ ሆይ” በሽፋን ገጹ ትኩረቱ “ከነ ብርጋዴር ጄነራል ተፈሪ በንቲ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ የአርባ አራት ዓመታት ጉዞ” የተቃኘበት መሆኑን ጠቁሟል፡፡

5. የሶማሌ ክልል በ“ጄል ኦጋዴን” ያከረማቸው አስር ሰዎችን መፍታቱ ተገለጸ፡፡ ከትናንት በስቲያ የተፈቱት የቀድሞ ሚኒስትር፣ ጋዜጠኞች፣ የፍርድ ቤት ሠራተኞች፣ የሕክምና ባለሙያ እና የመንግስት ሠራተኞች መሆናቸው ተነግሯል፡፡ ከሰሞኑ በክልሉ የተለያዩ ከተማዎች ርዕሰ መስተዳድሩ አብዲ ኢሌን የሚያወግዝ ትዕይንተ ሕዝብ ሲካሄድ ሠንብቷል፡፡

6. “ግሎባል አሊያንስ ፎር ዘ ራይት ኦፍ ኢትዮፒያንስ” የተሰኘው ግብረ ሠናይ ተቋም ከደቡብ ኢትዮጵያ ለተፈናቀሉ ዜጎች የገንዘብ ዕርዳታ አደረገ፡፡ ተቋሙ ለጌዲኦ፣ ወላይታ እና ጉራጌ ተፈናቃዮች ከግማሽ ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉ ነው የተገለጸው፡፡ በአንድ ሕዝብ መሐከል እንዲህ ያለ መጠፋፋት መፈጠሩ እንዳሳዘነውም ተቋሙ ገልጿል፡፡

7. ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ በሚካሄደው የ“ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ” (OMN) የአዲስ አበባ ቢሮ ምረቃ ዝግጅት ላይ ጃዋር መሐመድ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የገባው OMN የሀገር ቤት ቢሮውን በሚቀጥለው እሁድ በይፋ ሲያስመርቅ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ቄሮዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡ በዝግጅቱ ለጣቢያው ማጠናከሪያ የገቢ ማሰባሰቢያ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከወዲሁ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተማዎች ገንዘብ አሰባሳቢ ኮሚቴዎች ተቋቁመው በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡

8. የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትሱ ዱባይ ፖርትስ ከጅቡቲ መንግስት ጋር በነበረው የወደብ አስተዳደር ውዝግብ በፍርድ ቤት አሸነፈ። በለንደን ዓለማቀፍ ችሎት ውሳኔ መሰረት ጅቡቲ የዱባይ ፖርትስን ስምምነት ስርዛ ማባረሯ ህጋዊ አይደለም። ስለዚህም ድርጅቱ ከጅቡቲ መንግስት ጋር የነበረው ውል አሁንም ህጋዊ ስለሆነ ወደ ስራ መመለስ ይችላል ብሏል ፍርድ ቤቱ።
SHARE SHARE

Post Reply

Return to “Ethiopian Daily News .. ኢትዮ ዜናዎች”