መራር ቀልዶች!! (አለማየሁ ገላጋይ!)

User avatar
Ethiopian News
Leader
Leader
Posts: 967
Joined: 19 Aug 2009 17:01
Contact:

መራር ቀልዶች!! (አለማየሁ ገላጋይ!)

Unread post by Ethiopian News »

መራር ቀልዶች!! (አለማየሁ ገላጋይ!)
________________

……ሰኔ 1/1997 ዓ.ም የተቀሰቀሰው የአዲስ አበባ ነዋሪ አመፅ የ 26 ይሁን የ 36 ሰዎች ህይወት ቀጥፎ አለፈ። ህይወትን የቀመሳት በሙሉ የአንድ ሰው ህይወትም ቢሆን በምንም የማይተካ ዋጋ እንዳላት ይረዳል። የማቾቹ ቁጥር አያጣላንም ለማለት ነው።
ከዚህ የአዲስ አበቤዎች ሐዘን በስተጀርባ ምሬት ላይ የፈሉ ቀልዶች ስር ለስር መርመስመሳቸው አልቀም። ህዝቡ የሟቾቹን ቁጥር "36 ነው" ሲል መንግስት ደግሞ "26 ነው" በሚለው አቋሙ ፀንቶ እሰጥ አገባው በደራበት ሰሞን አንዱ እንዲህ አለ አሉ:–
"የተፈፀመው ግድያ ተጭበርብሯልና ይደገም!!"
*ቀላጁን አናውቀውም። ብናውቀውም አንቀየመውም። እንደውም ሀዘንና ጥቃት የሚፈጥረው የህዝብ ቁጣ ወደሌላ አቅጣጫ ቀይሮታልና ባለውለታችን ነው። ወይም ማህበራዊ ሳይንቲስታችን። ፍሬድሪክ ኒቼ ይሄን በተመለከተ "Birth of Tragedy" በሚል መፅሐፉ "ሐዘንና መከራን የቀልድ መነሻ ማድረግ ያስፈልጋል። ካልሆነ ማበድ ይከተላልና" ይለናል። ይሄንን እውነት ነው "ሳይንቲስታችን" በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ያደረገው።
___________\\\\_________
ቀልድ ለተአማኒነት አይገዛም ቢባልም ትንሽ የማይባል እውነታ ግን ሊኖረው ግድ ይለል። ለዚህም ይመስላል ቀጣይዋ የአዲስ አበባ ቀልድ ለቂርቆስ ልጆች መሰጠቷ። ለቦሌ ልጆች ብትቸር ኖሮ ከአስቂኝነቷ ይልቅ ተጠየቋ/መፋለሱ ይጎላና "እንዴት?" የሚል ጥያቄ ይነሳ ነበር። ቀልዷን እንይ……
……የሰኔ አንዱን አመፅ ለመበተን ፖሊስ ውሃ ተጠቅሞ ነበር ይባላል። ፖሊስ የውሃ ጅራፉን ደግኖ አመፅ አራማጆችን ለማጥቃት ፖሊስ ከተንቀሳቀሰባቸው አካባቢዎች አንዱ ቂርቆስ ነበር። ታዲያ ሰብሰብ ያሉ ወጣቶችን ያየው ፖሊስ ወጣቶቹን ለመበተን የውሃውን ጅራፍ ሲከፍት የቂርቆስ ልጆች አስበውበት ኖሮ ልብሳቸውን አውልቀው ከኪሳቸው ሳሙና በማውጣት ሰውነታቸውን መታጠብ ጀመሩ።
*እዚህ ቀልድ ውስጥ ጥቃትን የማለዘብ ዓለማ ብቻ አይደለም የሚታየው ኢኮኖሚያዊ ምፀትም አለ። ንፅህናን ለመጠበቅ እንኳ ውሃን የነሳ ድህነት! እስኪ ይታያችሁ በድህነት ይቀለዳል!? ያውም ነባሩን የድህነት እውነታ አጋኖ። ግን እንስቀለን። ምክንያቱም አፈጣጠራችን ወለፈንድነት (Paradoxy) አለበትና በድህነት እንስቃለን፣በነፃነት ማጣት እንስቃለን፣በባርነት እንስቃለን፣በረሃብ እንስቃለን፣በጥማት እንስቃለን፣በበሽታ እንስቃለን……በእነዚህ ችግሮች መጥፋትና በፍስሃ ላይ ከምንስቀወ በላይ በመከሮቹና በመከረኞቹ ላይ እንስቃለን። ይሄም ሲደረግ የኖረ የሰው ልጅ እውነት ነው።
_____________\\\\\_________________
ምንጭ መፅሐፍ :– ኢህአዴግን እከሳለሁ
በደራሲና ሐያሲ አለማየሁ ገላጋይ!

Source:
Seyfedin Musa
Facebook
Post Reply

Return to “Jokes and Funny stuff ...ቀልዶች እና አዝናኝ ርዕሶች”